ዶ/ር ዳንኤል ተፈራ፤

የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር፤ ኤመረተስ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ምኒስትር፤ ዶ/ር አቢይ አህመድ፤ በ6/18/18 ከህዝብ ተወካዮች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን መልስ አዳምጫለሁ። ጠቅላይ ምኒስትሩ ለሰጡት መልስና ላቀረቡት ገለጻ አስተያየቴን እንደሚከተለው ለማቅረብ አወዳለሁ።

አንደኛው የመደመር ፖለቲካ ያሉት ላይ ያተኩራል። ጠቅላይ ምኒስትሩ ሀገሪቱ አሁን የደረሰችበት ሁኔታ አደገኛ በመሆኑ የሀሳብ ልዩነቶች በሰላማዊና በቀና መንፈስ እንዲስተናገዱ ሀሳብ አቅርበዋል። ይህን ሀሳብ ያቀረቡት፤ ለተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆን ለራሱ ለገዢው መንግስትም ጭምር ነው።

ጠቅላይ ምኒስትሩ ሁሉን የሚያሳትፍ የፓለቲካ መስክ በመፍጠር እስከ ዛሬ የነበረውን አምባገነናዊ የፖለቲካ ባህል ለመቀየር መነሳታቸው ከዚህ በፊት ከታየው ልምድ የተለየ መሆኑን ያመለክታል። በኢትዮጵያ ባህል፤ ከፍርሀት የተነሳ፤ ሀሳብን በነፃ መግለጽና መመራመር የተለመደ ነገር አይደለም። ስለዚህ፤ ሀሳብ የሚገለጸው በአመጽ ወይም በተንኮል መንገድ ነው።

ሁለተኛው አስተያያቴ ክልልን በተመለከተ ይሆናል። በተለያዩ ክልሎች በየጊዜው ለሚፈጠሩት ግጭቶች መንስኤው ምን እንደሆነ ሲጠየቁ፤ መንስኤው ጥላቻ ነው ብለዋል።  በኢትዮጵያ ውስጥ ጥላቻ ረጅም ታሪክ አለው በማለትም ምሳሌዎች ጠቅሰዋል።

ይሁንና፤ ከጥላቻ ይልቅ ቂምበቀል ነው በኢትዮጵያ ውስጥ ረጅም ታሪክ  ያለው። የጠቀሷቸው ምሳሌዎች የቀድሞ መሪዎች የፈጸሟቸው የቂም በቀል ሥራዎች ናቸው። ጠቅላይ ምኒስትሩ የተፈጸሙትን ግፎች በይፋ መናገራቸው፤ ለህዝቡ በተለይ ለአዲሱ ትውልድ ትልቅ ትምህርት ይሰጣል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪኩ የሚታወቀው በመጠላላት ሳይሆን በእንግዳ ተቀባይነቱና በ’አብረን እንብላ’ ባይነቱ ነበር። የእርስበርስ ጥላቻን ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ያነገሰው የዘር ክልል ነው ማለት ይቻላል። ለምሳሌ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት ያገለገሉት የራሱ የሆኑ ክፍለሀገሮች ነበሩት። በዚያን ጊዜ የአሁኑ ዓይነት ግጭትና ጥላቻ አልነበረም።

ክልል የተባለው ያስተዳደር አወቃቀር፤ ኢትዮጵያ ላይ አስጊ ሁኔታ ማስከተሉን ጠቅላይ ምኒስትሩ በጉዳዩ ከሚሰጡት አስተያየት መገመት ይቻላል። በመጀመሪያ፤ ችግሩን የወሰን አከላለል ችግር አድርገው ነው ያቀረቡት። ቀጥሎም፤ ችግሩን የሚያጠና ኮሚቴ ይቋቋማል ብለዋል።

ነገር ግን፤ ዋናው ችግር እራሱ ክልል የተባለው አወቃቀር ነው። ለምሳሌ፤ ቀድሞ የጎንደር የነበረው መሬት ለምን ዛሬ  በትግሬ ስር ተካለለ? ሶማሌና ኦሮሞ ሀረርጌ የሚባል ሀገር ነበራቸው። ለምን እንዲከፋፈሉ ተደረጉ? ጠቅላይ ምኒስትሩ እንዳሉት ሳይሆን፤ መጠናት ያለባቸው እነዚህ ጥያቄዎች ናቸው።

ሦስተኛው አስተያየቴ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በተመለከተ በሰጡት መልስና ባደረጉት ገለጻ ላይ ነው። በመጀመሪያ፤ በአሁኑ ሰዓት ሀገሪቱ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ እጥረት ውስጥ የምትገኝ መሆንዋን ጠቅላይ ምኒስትሩ አልሸሸጉም። ስለዚህ የመንግሥት ሞኖፖሊዎችን ወደ ባለአክሲዮን ኩባንያዎች በመለወጥና የውጪ ንግዱን ክፍል በማጠናከር የምንዛሪ ምንጭ ለመፍጠር መታቀዱን ገልጸዋል።

ይሁንና፤ የውጪ ምንዛሪ እጥረት ከጠቅላላው ኢኮኖሚ ተነጥሎ ሊታይ አይችልም። ኢኮኖሚው እንኳን ለውጪ ንግድ ይቅርና ለውስጥም ፍጆት በቅጡ ማምረት አይችልም። ስለዚህ፤ ጠቅላይ ምኒስትሩ፤ ኢኮኖሚውን ለማሻሻል ታቅደዋል ካሏቸው መካከል የመስኖ እርሻ ልማትና የከብት እርባታ ተጠቅሰዋል። ለእርሻ ትኩረት መስጠታቸው ተገቢ ነው። ነገር ግን፤ የእርሻ ዋና ማምረቻ መሬት ሆኖ ሳለ፤ ጠቅላይ ምኒስትሩ ህዝቡን የመሬት ባለቤት ስለማድረግ የተናገሩት ምንም ነገር የለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ጠቅላይ ምኒስትሩ ኢትዮጵያ የምትመራው በልማታዊ መንግስት ነው፤ ዓላማውም የካፒታሊስት ስርአት መገንባት ነው ብለዋል። ለማስታወስ ያህል፤ ልማታዊ መንግሥት የሚለው ቃል የተፈጠረው በምእራባዊያን የልማት ባለሙያዎቸ ሲሆን፤ ትርጉሙም ልማትን በዋናነት የሚመራ መንግሥት ማለት ነው።

ለልማታዊ መንግሥት እንደምሳሌ ተደርገው የሚጠቀሱት የደቡብ ምስራቅ እሲያ ሀገሮች ናቸው። እነዚህ ሀገሮች በፍጥነት ሊለሙ የቻሉት ልማቱን መንግሥት በዋናነት ስለመራው ነው ብሎ ማመን ሌላ ጥያቄ ያስከትላል። ይኸውም፤ ልማት በመንግሥት ዋናነት የሚመጣ ከሆነ ለምን ኢትዮጵያ ሳትለማ ቀረች?

ከላይ የተጠቀሱት ሀገሮች በፍጥነት ሊለሙ የቻሉት፤ ለብዙ ዘመናት ህዝቦቻቸውን ጨቁኖ ይዞ የነበረውን የጉልተኛ ስርአት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ (በአሜሪካን ከፍተኛ ግፊት) በማጥፋታቸው ነው። ይህ ሽግግር፤ በድህነት ይማቅቅ የነበረውን ሰፊ ህዝብ የመሬት ባለቤትና ባለገቢ እንዲሆን አድርጓል። ይህም የውስጥ ገበያ በመፍጠሩ፤ እንዱስትሪና ንግድ በፍጥነት ሊስፋፉ ችለዋል።

ጠቅላይ ምኒስትሩ አንዱ ዓላማቸው መዋለንዋይ ከውጪ ወደኢትዮጵያ እንዲፈስ ማበረታታት ነው ብለዋል። ይህ የሚደገፍ ሀሳብ ነው። ይህን ዓላማ ሊያጨናግፉ የሚችሉ መሠረታዊ ችግሮች እንዳሉ ግን መዘንጋት የለበትም። አንደኛ፤ የኢትዮጵያ ገበያ በጣም ትንሽ ነው። ካፒታል በሰፊው የሚፈስው ወደ ሰፋፊ ገበያዎች እንጂ ወደ ጠባብ ገበያዎች አይደለም። ለምሳሌ፤ ወደደቡብ አፍሪካ ወይም ኬንያ በቀላሉ ይገባል ከኢትዮጵያ ይልቅ። ስለዚህ፤ ኢትዮጵያ በመጀመሪያ የውሰጥ ገበያዋን ማዳበርና ማስፋት ይኖርባታል ማለት ነው።

በውስጥ ገበያ ላይ ማተኮር በየጊዜው በውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚፈጠረውን ችግር ይቀንሳል። ለምሳሌ፤ ዛሬ ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅስው የኮንስትራክሽን ሥራ ሲሆን፤ እቃው ግን የሚመጣው በብዛት ከውጭ ነው። ገንዘቡ ወደውጪ ይፈሳል ማለት ነው። ከኮንስትራክሽን ጋር ተያይዞ የሀገሪቱን ካፒታልና የውጪ ምንዛሪ ያሟጠጡት ከአቅም በላይ የሆኑ በብዛት በብድር የተሠሩ ምርትአልባ ፕሮጀክቶች ናቸው።

እነዚህን ብድሮች ለመክፈል ያለውን የውጪ ምንዛሪ ችግር ጠቅላይ ምኒስትሩ ጠቅሰዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ ያልጠቀሷቸው ከብድር ጋር የተያያዙ ሌሎች ችግሮችም አሉ። አንደኛ፤ ኢትዮጵያ ከቻይና ስትበደር የኖረችው በጣም ከፍተኛ በሆነ ወለድ ነው። ሁለተኛ፤ ብድሩ የሚያለማው የቻይናን እንጂ፤ የኢትጵያን ኢኮኖሚ አይደለም። ሠራተኛውም እቃውም ከቻይና ነው የሚጎርፈው።

የመጨረሻው አስተያየቴ፤ ጠቅላይ ምኒስትሩ የአፍሪካን ቀንድ በተመለከተ ባቀረቡት ሀሳብ ላይ ይሆናል። ጠቅላይ ምኒስትሩ ስለአፍሪካ ቀንድ ህብረት ጠቃሚነት የሰጡት ገለጻ በህዝቡም ሆነ በጎረቤት ሀገሮች በኩል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በተለይ ለኤርትራ የሰላም ጥሪ ማቅረባቸውንና መልስ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች የጋራ ገበያ፤ ለቀጠናው ህዝቦች ብልጽግና እንዲሁም ሰላም ጠቃሚ መሆኑን ጠቅላይ ምኒስትሩ  አስረድተዋል። ኢትዮጵያና ኤርትራ ጠላት በከለለው ድንበር ላይ ካተኮሩ፤ እንደገና ለውጪ ኃይሎች ሲሳይ ነው የሚሆኑት። ስለዚህ፤ የሁለቱንም ኢኮኖሚ ሊጠቅም የሚችለው በመካከላቸው ወሰን ማቆም ሳይሆን፤ ወሰኑን ማንሳት ነው።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብትና የህዝብ ብዛት ያላት ሀገር ናት። ቢሆንም፤ የነፍስ ወከፍ ገቢዋ ከሁሉም የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ያነሰ ነው። ኢትዮጵያ፤ ኤርትራንም ይሁን ሌሎቹን የቀንድ ሀገሮች ለመሳብና የጋራ ገበያ ለመመሥረት የምትችለው፤ የዳበረ ኢኮኖሚ ሲኖራት ብቻ ነው። ስሊዚህ፤ በዘር ክልል የተከፋፈለውን የኢትዮጵያን ገበያ በመጀመሪያ አንድ በማድረግ የውስጡን ኢኮኖሚ በፍጥነት ማሳደግ ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።