ዶ/ር ዳንኤል ተፈራ
የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር፤ ኤመረተስ

በዚህ ጽሁፍ፤ ባለፈው ሰኞ (4/2/18) በኢትዮጵያ ፓርላማ ውስጥ የቀረበውን የአዲሱን ጠቅላይ ማኒስትር ንግግርና የህዝቡን ጥያቄዎች ባጭሩ ለማነጻጸር እሞክራለሁ። ይህን ሳደርግ፤ የጠቅላይ ምኒስትሩ ንግግር የገዢውን ቡድን አቋም እንደሚያንጸባርቅ በመረዳት ነው።

ላለፉት ሦስት አመታት፤ የህዝብ እንቅስቃሴዎች በሀገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች ተነስተዋል። እነዚህ ህዝባዊ ትግሎች የጋራ የሆኑ ጥያቄዎችን አንስተዋል። አንደኛው ጥያቄ፤ በዘር (ብሔር) መከፋፈል አንፈልግም የሚል ነበር።

የኢትዮጵያ በዘር መከፋፈል፤ ከፍ ያለ ጉዳት በህዝቡ ላይ አድርሷል። በእርስ በርስ የጥላቻ ግጭቶች ምክንያት ብዙ ሰው ሞቷል። ብዙ ንብረት ጠፍቷል። ብዙ ሰው ተፈናቅሏል።
በገዛ ሀገሩ ብዙ ህዝብ ስደተኛ ሆኖ እንዲኖር ተገዷል። ለምሳሌ፤ አሁን በቅርቡ እንኳን፤ ቁጥራቸው ከመቶ ሺህ በላይ የሚገመት ኦሮሞዎች፤ የትውልድ ሀገራቸውን ሐረርጌን (ያሁኑ የሱማሌ መንግሥት) ጥለው ሸሽተዋል።

ይህ ሁሉ ጥፋት የተፈጠረው ሀገሪቷ በዘር ከተከፋፈለች በኋላ ነው። ከዚያ በፊት ግን፤ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚታወቀው አብሮ በመኖርና በእንግዳ ተቀባይነቱ ነበር።

የጠቅላይ ምኒስትሩ ንግግር፤ ስለአብሮነት ያነሳል። ነገር ግን፤ በብሔር መከፋፈል የአብሮነት ጠንቅ መሆኑን መቀበል አይፈልግም። ስለሆነም፤ ከኋላቀር ብሔርተኝነት ይልቅ ሌለ ዘመናዊና ሰላማዊ አስተሳሰብ እንዳለ ማየት አልቻለም።

የገዢው ቡድን ፍላጎት፤ ኢትዮጵያን ወደዲሞክራሲ ከማሸጋገር ይልቅ፤ ህብረብሔራዊ ኢትዮጵያ መመሥረት መሆኑን የጠቅላይ ምኒሰትሩ ንግግር ይጠቁማል። ይሁንና፤ እስካሁን የታዩት ብሔርወለድ ጥፋቶች ከግንዛቤ ከገቡ፤ ህብረብሔር ኢትዮጵያ፤ ዛሬም ይሁን ወደፊት፤ ሰላምና አንድነት ይኖራታል ብሎ ለማመን ያዳግታል።

በሌላ በኩል፤ ኢትዮጵያዊነት የአንድነት መሠረት ነው የሚል ሀሳብ በጠቅላይ ምኒስትሩ ንግግር ውስጥ ተደጋግሞ ተነስቷል። ይሁንና፤ በህገመንግሥቱ መሠረት የህዝቡ ዋና መገለጫ፤ ብሔር እንጂ ኢትዮጵያዊ ዜግነት አይደለም።

ስለዚህ፤ ኢትዮጵያዊነት የተጠቀሰበት ምክንያት ግልጽ አይደለም። ኢትዮጵያዊነት የመላው ህዝብ የአንድነት መሠረት እንዲሆን ከተፈለገ፤ ማንኛውም ዜጋ በሀገሩ ነፃነትና ሀብት ተጠቆሞ መኖር መቻል አለበት።

ሁለተኛው የህዝቡ ጥያቄ፤ እራሳችን በመረጥነው መንግሥት ለመተዳደር እንፈልጋለን የሚል ነው። ይህ ትክክለኛ የዲሞክራሲ ጥያቄ ሆኖ ሳለ፤ የጠቅላይ ምኒስትሩ ንግግር፤ ዲሞክራሲ በሀገሪቱ ውስጥ አሁን እንዳለ አድርጎ ያቀርባል።

“ዲምክራሲ በሀገሪቱ ውስጥ አለ። ማዳበር ብቻ ነው የሚጠይቀው። የዳበረ ዲምክራሲን ለመገንባት ተቃዋሚዎች እኛን እርዱን” ይላል ሌላውን እንደአላዋቂ በመቁጠር፤ የጠቅላይ ምኒስትሩ ንግግር።

በመጀመሪያ፤ ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ ውስጥ አለ ብሎ በማስረጃ ለመግለጽ አይቻልም። ዲሞክራሲ የሚለካው ምርጫ በማካሄድ አይደለም። የዲሞክራሲ ዋና መገለጫ፤ የመቃወም መብት መኖር ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ ካለ፤ ለምንድነው ታድያ ተቃዋሚዎች ሀሳባቸውን በነፃ ለመግለጽ የማይፈቀድላቸው? ሀሳባቸውንም ለመግለጽ ከደፈሩ፤ ለምንድነው የሚታሰሩት? የሚደበደቡት? የሚገደሉት?

የገዢው ቡድን፤ የብሔርተኞችና የኮሚንስቶች ስብስብ ሆኖ ሳለ፤ እራሱን የዲሞክራሲ ሓዋርያ አድረጎ በመሾም፤ የፓለቲካ ተቃዋሚዎችን ዝቅ አድርጎ ይመለከታል። የራሱን ሀሳብ ብቻ እንዲሰሙለት ይፈልጋል። ስለዚህ፤ እራሱን ሊያሻሽል አልቻለም። መጠን የለቀቀ ገታራነቱ፤ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ወደ ትጥቅ ትግል እንዲገቡ አስገድዷቸዋል።

ሦስተኛውና ዋነኛው የህዝቡ ጥያቄ፤ መሬት ያላግባብ ተነጥቀናል የሚለው ነበር። የጠቅላይ ምኒስትሩ ንግግር ግን፤ ስለመሬት ምንም ነገር አያነሳም።

በኢትዮጵያ ውስጥ የህዝቡ ዋና ሠርቶ ማደሪያ መንገድ መሬት በማረስ ነው። መሬት የሀብት ምንጭ ነው። ስለዚህ፤ መሬት የጥቂት ሰዎች ወይም የመንግሥት ብቻ የግል ንብረት መሆን የለበትም።

ኢትዮጵያ ውስጥ፤ ከዛሬ 45 ዓመታት ጀምሮ፤ መሬት (አረንጓዴው ወርቅ፤ በዛሬው ስሙ)፤ የመንግሥት፤ ማለትም የገዢ መደብ፤ ሞኖፓሊ ነው። ህዝቡ ግን፤ የመንግሥት መሬት ተከራይ በመሆን በድህነት እየማቀቀ ነው የሚኖረው። ጉልተኛው መንግሥት ባስፈለገው ሰዓት ያከራየውን የመጠቀም መብት መልሶ መውሰድ ይችላል።

የጠቅላይ ምኒስትሩ ንግግር፤ ስለድህነት ማሻሻል ያወሳል። ነገር ግን፤ መፍትሄ ተብሎ የተጠቀሰው አዲስ ነገር አይደለም። ያው እንደተለመደው የውጪ ድርጅቶች፤ እራሳቸውንና የገዢውን ቡድን ለመጥቀም ብለው ያወጡት “የልማት” ፖሊሲ ነው።

እርሻ ሰማይ ላይ ይታረስ ይመሰል፤ እነዚህ ድርጅቶች ስለመሬት ማከፋፈል ጉዳይ በፍጹም አያነሱም። አንዳንድ ምሁራንም “መሬት ማከፋፈል አያስፈልግም። ቻይናን ተመልከቱ” ይላሉ። ይህ ዓይነቱ አባባል ጠቃሚ እውቅት አይደለም። ይህ አስተሳሰብ፤ እነዚህ ምሁራን፤ ቻይናንም ይሁን ኢትዮጵያን ጠንቅቀው አለማጥናታቸውን ነው የሚያጋልጠው።

ኢትዮጵያ ውስጥ እርሻ እንዲለማ፤ ድህነትም እንዲሻሻል ከተፈለገ፤ በመጀመሪያ የህብረተሰቡ ደረጃ መስተካከል ይኖርበታል። ስለዚህ፤ ድሀውን ህዝብ ባለንብረት ማድረግ ያስፈልጋል። ማለትም፤ መሬት ከመንግሥት ሞኖፖሊ ተላቆ፤ ለህዝቡ በባለቤትነት፤ በፍህታዊ መንገድ መከፋፈል አለበት።

የጠቅላይ ምኒስትሩ ንግግር ልማታዊ ዲሞክራሲ የሚባለውን የገዢውን መደብ መመሪያ ያነሳል። “ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ልማት ላይ ማተኮር አለባት፤ ከዚያ በኋላ ዲሞክራሲ ራሱ በራሱ ይመጣል” ለማለት ይመስለኛል። ይህ ፖለቲካ እንጂ፤ ልማት አይደለም። ዲሞክራሲም አይደለም። አሁን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ በሚገኝበት በጣም አሳሳቢ በሆነ የመሬት አጥነት ደረጃ፤ ልማት ማምጣት ይቻላል ለማለት ያዳግታል።

ለማጠቃለል ያህል፤ የጠቅላይ ምኒስትሩ ንግግር የህዝቡን ጥያቄዎች መልሷል ለማለት አይቻልም። ጥያቄዎቹ ጥልቅ እንደመሆናቸው ሁሉ፤ ሰፋ ያለ ዘመናዊ አስተሳሰብን፤ ምክክርንና መደማመጥን ይጠይቃሉ። ስለዚህ፤ ገዢው ክፍል፤ ከሁሉም የፖለቲካና የህብረተሰቡ አካላት ጋር በእኩልነትና በቅን መንፈስ ለመወያየትና መፍትሄ ለመፈለግ ፈቃደኝነቱን ማሳየት ይኖርበታል።