ዶ/ር ዳንኤል ተፈራ
የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር፤ ኤመረተስ

ላለፉት ሀያሰባት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተደራጀው በዘጠኝ ክልላዊ መንግሥታት በሚባሉ አማካኝነት ነው። ይህ አከላለል በኢኮኖሚው ላይ ጉዳት እንጂ ጥቅም አላመጣም። ለምሳሌ፤ የሀገሪቱን የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ሀብት አባክኗል። ገበያዎች እንዲከፋፈሉ በማድረግ ህዝቡን በታትኗል። ስለዚህ፤ ዛሬ በሀገሪቱ ውስጥ ሰላምና የረባ ኢኮኖሚ አለመኖር፤ እንዲሁም የሥራ ዕድል መጥፋት ከክልል አደረጃጀት ጋር ይያዛል።

በመጀመሪያ መጠቀስ ያለበት ነገር አለ። ይኸውም፤ የዘር ክልል ከመምጣቱ በፊት፤ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ጥቅም የተሳሰረች አንድ ሀገር፤ አንድ መንግሥት ነበረች። ለምሳሌ፤ ድሮ የወለጋ የኢኮኖሚ ትስስር ከጎጃም ጋር ነበር። ዛሬ ወለጋ፤ ኦሮሚያ በሚሉት ውስጥ ተካሏል። ጎጃም ደግሞ የአመራ ክልል ተደርጓል።

ስለዚህ፤ በሁለቱ ክፍለሀገሮች መካከል ለዘመናት የነበረው የኢኮኖሚ ግንኙነትና ጥቅም እንዲቋረጥ ተደርጓል ማለት ነው። በዚሁ አንፃር፤ ዛሬ በኦሮሚያ ውስጥ የተካለለው ቦረና፤ ለብዙ ዘመናት በጥቅም ተሳሰሮ የኖረው ከአካባቢው ህብረተሰቦች ጋር እንጂ፤ በርቀት ካለው ከኢሉባቦር ወይም ከወለጋ ጋር አልነበረም።

ሌላው ክልል ያስከተለው ችግር፤ በክልሎቹ መከካል የተፈጠረው የስፋትና የተፈጥሮ ሀብት ልዩነት ነው። ለምሳሌ፤ ሀረሪ የሚባለው ክልል በጣም ከማነሱ የተነሳ፤ በመልክአ ምድር ሰሌዳ ላይ ሞኖሩን ማወቅ ያዳግታል። ስለዚህ፤ የህዝቡ ቁጥርና ፍላጎት በጨመረ ቁጥር፤ የመፈናፈኛ ቦታና የሥራ እድል ስለማይኖር፤ ድህነት ይባባሳል ማለት ነው።

የስፋት ማነስ ብቻ ሳይሆን፤ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብትም የሚያስከትለው የኢኮኖሚ ችግር አለ። ምክንያቱም፤ የተፈጥሮ ሀብት ካልተሠራበት ምርትአልባና ጥቅመቢስ ነው። ለምሳሌ፤ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት በብዛት ያለው ኦሮሚያና ደቡብ ብለው በሚጠሯቸው ክልሎች ውስጥ ነው።

ነገር ግን፤ ይህ ጥሬ ሀብት አልተሠራበትም። እነዚህ ክልሎች እንደስፋታቸውና የተፈጥሮ ሀብት መጠናቸው፤ በቂ የሰው ኃይልና ካፒታል የላቸውም። ይህ ሆኖ ሳለ፤ እነዚህ ቦታዎች ለሌላው በመከልከላቸው፤ በክልሎቹ ውስጥ የተፈጠረው የሰው ኃይልና የካፒታል ክፍተት ሊሟላ አልቻለም።

የክልል አደረጃጀት፤ ካፒታል እንዳይስፋፋ ከማድረጉ ጋር ተያይዞ፤ የሰውን ልጅ ከአንዱ ስፍራ ወደሌላው ስፍራ እንደልቡ ተዘዋውሮ የመሥራት ነፃነት ይከለክላል። አንድ ግለሰብ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት ቢፈልግ፤ የሕይወትም ይሁን የንብረት ዋስትና የለውም። “ከክልሌ ውጣልኝና ወደእራስህ ክልል ሂድ” ነው የሚባለው። ዛሬ፤ ነፃ የህዝብ መዘዋወር ይቅርና፤ አንደኛው ክልል ከሌላው ክልል አንዲት የድንጋይ ጠጠር እንኳን መውሰድ አይችልም።

የክልል አደረጃጀት ከመጣ በኋላ፤ የቀድሞ የገጠር ከተማዎች ዛሬ ቀዝቅዘዋል፤ አንዳንዶቹም ጨርሰው ጠፍተዋል። ለምሳሌ፤ በቀድሞው የሲዳሞ ክፍለሀገር፤ ታላላቅ የንግድ ከተማዎች የነበሩ፤ እነዲላና ይርጋጨፌ ተዳክመዋል። አለታ ወንዶ ሞቷል ማለት ይቻላል። የይርጋዓለም የአራዳው ሰፈር ንግድ በቦታውም የለ። ስደተኛ ሰፈር በቋፍ ነው ያለው።

የእነዚህ ከተማዎች መዳከም፤ ከዚህ በፊት በከተማና በገጠር መካከል የነበረውን የኢኮኖሚ ግንኙነትና ጥቅም እንዲቋረጥ አድርጓል። ለምሳሌ፤ አንድ ነጋዴ ወይም ሌላ ታታሪ ግለሰብ ገጠር ውስጥ ገብቶ መሬት በመግዛትና የራሱን መዋለንዋ በማፍሰስ ዘመናዊ እርሻ አልምቶ እራሱንና ህብረተሰቡን ለመጥቀም አይችልም።

ቀድሞ በተለያዩ ከተማዎች ይገኝ የነበረው የምርትና የሥራ እድል፤ ዛሬ ከአንድ የክልል ከተማ አያልፍም። በሰሜን ኢትዮጵያ፤ ባህር ዳር ውስጥ ያለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፤ በደብረ ማርቆስ፤ ጎንደርና ደሴ ላይ አይታይም። በደቡብ ኢትዮጵያ፤ ሀዋሳ ላይ ብቻ ነው ትኩረቱ ያለው። ይህም ቢሆን፤ የመዝናኛ እንዱስትሪን እንጂ የአካባቢውን ሰፊ የእርሻ ተሰጦ ያማከለ አይደለም።

የበፊት ክፍለሀገሮች ዋና ከተማዎች በመታጠፋቸው በህዝቡ ላይ የማያስፈልግ የገንዘብ ወጪና የሥራ ጊዜ መባከንን አስከትሏል። ለምሳሌ፤ የወለጋ ገበሬ ወይም ነጋዴ ጉዳይ ካለበት፤ አጠገቡ ያለውን ነቀምቴን ትቶ አዳማ ድረስ ለመሄድ ይገደዳል ማለት ነው። እንደዚሁም፤ የጎጃም ባለጉዳይ ደበረ ማርቆስን ትቶ ባህር ዳር ይሄዳል። የገሙ ጎፋውም፤ አርባ ምንጭ በመሄድ ፈንታ ሀዋሳ መሄድ ይኖርበታል።

የክልል ስርአት፤ ህዝቡ ለኑሮው በኢኮኖሚ ላይ ከመመካት ይልቅ የመንግሥት ጥገኛ እንዲሆን አደርጎታል። ኢኮኖሚ ቀርቶ መንግሥት ዋና የሥራ ፈጣሪ ነኝ ባይ ነው። ስለዚህ፤ በተለያዩ የክልል ከተማዎች የእንዱስትሪ መንደር ብሎ የሚጠራውን ይገነባል።

ይሁንና፤ የእንዱሰትሪ መንደር የራሱ የሆኑ ችግሮች አሉት። አንደኛ፤ የእንዱስትሪ መንደር ለመገንባት ከፍ ያለ ወጪ ይጠይቃል። ሁለተኛ፤ ሀገሪቱ ገንዘብ ስለሌላት፤ ከውጪ መበደር ሊኖርባት ነው። ብድሩ ደግሞ በርካሽ ዋጋ አይገኝም።

ገንዘቡ ቢገኝም፤ ሌላ ችግር አለ። ኢትዮጵያ በሥራ ላይ ያልዋለ ብዙ የሰው ጉልበት ቢኖራትም፤ ለእንዱስትሪ የሚሆን በቂ ጥሬ እቃ አታመርትም። ስለዚህ፤ ጥሬ እቃውን ከውጪ ማስገባት ይኖርባታል። ይህ እንደገና፤ ሰፊ የውጪ ምንዛሪ ክምችት ይጠይቃል።

ለመረጃ ያህል፤ የእንዱስትሪ መንደር ከቻይና የተወሰደ ሀሳብ ነው። ቻይና ካፒታል ከውጪ በማስገባት ለህዝቧ የሥራ እድል ለመፍጠር የቻለችው፤ ብዙውን ጥሬ እቃ እራስዋ በማምረቷና ያለበለዚያም ከውጪ ለመግዛት የሚያስችል ከፍ ያለ የውጪ ምንዛሪ ክምችት ስለነበራት ነው።

ባጠቃላይ፤ የእንዱስትሪ መንደር መገንባት የዘር ክልል ላስከተላቸው የኢኮኖሚ ችግሮች መፍትሄ ሊሆን አይችልም። የዘር ክልል፤ የሀገሪቱን ህብረተሰብ የሚጎዳ የሞኖፖሊ አደረጃጀት ስለሆነ፤ ነፃ ኢኮኖሚ ሊፈጥር የሚችለውን ምርትና የሥራ እድል ሊያስገኝ አይችልም።

ስለዚህ፤ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩት አሳሳቢ የኢኮኖሚና የሥራ አጥነት ችግሮች እንዲቃለሉ ከተፈለገ፤ ለሀያሰባት ዓመታት ህዝቡን በመከፋፈልና በማጠር የሥራ እንዲሁም የመዋለ ንዋይ ነፃነት የከለከለው የዘር ክልል ስርአት ከሀገሪቱ ጨርሶ እንዲወገድ መደረግ ይኖርበታል።