ዶ/ር ዳንኤል ተፈራ
የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር፤ ኤመረተስ

በአዲሱ ትውልድ የሚመራው ህዝባዊ እምቢተኝነት በፈጠረው ግፊት፤ ያላግባብ ለብዙ ዓመታት የታሰሩ የፓለቲካና የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቾች ሊፈቱ ችለዋል። ተፈቺዎቹ እንደገለጹት ከሆነ፤ አሁንም ብዙ ሰዎች በእስር እየተንገላቱ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ እምቢተኝነት፤ ለሕወሀት ገዢዎችና ለተቀሩትም ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ትምህርትን ያዘለ ነው። ይህም ማለት፤ ከእንግዲህ በኋለ የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ ሰው ወይም ጎራ ለመገዛት አይፈልግም። እራሱን በራሱ ለማስተዳደር ወደሚችልበት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር ነው ፍላጎቱ።

ይህ ከሆነ፤ የሕወሀት ገዢዎች በሥልጣን ለመቆየት የሚወስዱት እርምጃ እንዲሁም በተቃዋሚ ፖለቲከኞች መካከል ሥልጣን ለመያዝ የሚደረገው ፉክክር፤ ለኢትዮጵያ ጉዳት እንጂ ጥቅም አይኖረውም። ህዝቡን በመከፋፈል አገሪቱን ለማያቋርጥ የርስበርስ ብጥብጥ ነው የሚዳርጋት።

ስለዚህ፤ የሕወሀት ገዢዎችም ሆኑ ተቃዋሚዎች፤ በአሁኑ ሰዓት የሚጠበቅባቸው አንድ ነገር አለ። ይኸውም፤ ከህዝቡ ጎን በመሆን ኢትዮጵያ ወደ እውነተኛ ዲሞክራሲ እንድትሸጋገር በቅን መንፈስ በመተባበር በቅድሚያ መደረግ ያለባቸው ጉዳዮች ላይ ማተኮር ነው።

“ዲሞክራሲ” የሚለው ቃል በተለያዩ ክፍሎች ሲጠቀስ ይሰማል። ይሁንና ዲሞክራሲ ባህል እንጂ በማንበብ ብቻ ሊረዱት የሚችሉት ነገር አይደለም። ዲሞክራሲ ምርጫ ማካሄድም አይደለም። እኩልነት በሌለበት ህብረተሰብ ውሰጥ ምርጫ (ነፃም ይሁን አይሁን)ቢካሄድ ዲሞክራሲ ሊመጣ አይችልም።

ኢትዮጵያ ወደአዲሱ የዲሞክራሲ ባህል ለመሸጋገር የምትችለው፤ ሁሉም ክፍሎች በሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ በአንድነት በመነጋገርና በመሸጋሸግ ጥቅማቸውን ማስከበር ሲችሉ ነው። ማንኛውም ክፍል ቢሆን የፈለገውን ሁሉ ማግኘት አይችልም። የሚያገኘው ጥቅም ግን ይኖራል፤ አብሮ በመሥራት።

ስለዚህ አሁን በቅድሚያ፤ በተለይ ከዚህ በታች በተጠቀሱት የሀገሪቱ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማካሄድ ቋሚ ስምምነቶች ላይ መድረስ ያስፈልጋል።

በመጀመሪያ፤ ለ27 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያ በዘር ክልል በመከፋፈልዋ፤ እኩል ዜግነት በሀገሪቱ ውስጥ ሊሰፍን አልቻለም። በተጨማሪ፤ የክልል ወሰኖች በአብዛኛው ህዝብ ተቀባይነት ስለሌላቸው፤ በተለያዩ ቦታዎች የግጭትና የጥፋት መንስኤዎች ሆነዋል።

ስለዚህ፤ ኢትዮጵያ በክፍለሀገራዊ የፌደራል አስተዳደር መሠረት ትዋቀር ወይስ አሁን ባለው ክልላዊ ፌደሬሽን ትቀጥል? የሚለው ጥያቄ ስምምነት ላይ መድረስን ይጠይቃል።

ሁለተኛው መሠረታዊ ጉዳይ፤ ብሄራዊ አንድነትን የሚመለከት ነው። ለብዙ ዘመናት የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ዋልታዎች ሆነው ያገለገሉት የአማራ/ትግሬ ባህል፤ የኦርቶዶክስ ክርስትያን ሃይማኖትና የአማርኛ ቋንቋ ናቸው።

ኢትዮጵያ የብዙ ህዝብ ባህሎች፤ ቋንቋዎችና ሃይማኖቶች አገር እንደመሆንዋ መጠን፤ ብሄራዊ አንድነትዋ ሁሉን አቀፍና የጠነከረ ሊሆን የሚችልበት መንገድ ሊፈለግ ይገባል።

ለምሳሌ፤ ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ሁሉ የታደለች ሀገር ናት። ይህም ማለት፤ በመላው ሀገሪቱ ውስጥ ለብዙ ዘመናት መገናኛ ሆኖ የቆየ የራስዋ የአማርኛ ቋንቋ አላት። በተጨማሪም፤ በአንዳን ቦታዎች ብቻ በሰፊው የሚነገሩ፤ እንደ ኦሮምኛ ያሉ ቋንቋዎች አሏት። እነዚህ ቋንቋዎች ከአማርኛ ጋር ቢታቀፉ፤ የኢትዮጵያን አንድነት በይበልጥ ሊያጠናክሩ ይችላሉ።

ሦስተኛው መሠረታዊ ጉዳይ፤ የመሬት ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ፤ መሬት የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ አይደለም። የነፃነትና የእኩልነትም ጉዳይ ነው።

በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን፤ አርባ አምስት ከመቶ የሆነው ገበሬው ህዝብ (በተለይ በሲዳማ/ኦሮሞ ክፍለሀገሮች) የመሬት ባለቤት አልነበረም። የእኩል አራሽ በመሆን፤ ሌላውን የባለመሬት ክፍል እያገለገለ ነው የኖረው።

ከዚያም በኋላ፤ በወታደራዊው መንግሥት ጊዜ፤ የእኩል አራሽነት ቀርቶ፤ ገበሬው ህዝብ በእጅ እራሹ መሬት አርሶ የመጠቀም መብት ብቻ ተፈቀደለት። ባለቤትነት ግን አልተሰጠውም።

የገጠርና የከተማ መሬቶች በሙሉ በመንግሥት እጅ ገቡ። ስለዚህ በመሬት የሚያዙት የመንግሥት ሥልጣን የጨበጡት ብቻ በመሆናቸው፤ እነርሱ የበላይ ሲሆኑ፤ ህዝቡ ደግሞ የበታች ሆኖ እንዲኖር ተገደደ።

የሕወሀት ገዢዎች ከተተኩም በኋላ፤ በመሬት የመጠቀም መብት ወደኪራይ እንዲለወጥ ተደረገ። በዚህ መሠረት፤መንግሥት የመሬት አከራይ ጉልተኛ ሲሆን፤ ህዝቡ ደግሞ ተከራይቶ አዳሪ ጪሰኛ ሆኖ ያለዋስትና እንዲኖር ሆነ።

እንዲህ በመሆኑም፤ የመንግሥት ባለሥልጣኖች በገጠርና በከተማ ህዝቡን እንደፈለጉት ከመጠቀም መብቱ በማፈናቀል፤ መሬቱን ለሌላ በጨረታ እያከራዩና እየሸጡ እራሳቸውን ማክበሪያ አደረጉት።

እዚህ ላይ፤ አንድ መጠቀስ ያለበት ነገር አለ። በመሬት የመጠቀም መብት ማለት የባለቤትነት መብት ማለት አይደለም። ከላይ እንደተጠቀሰው፤ ከጉልተኛ ስርአት አይለይም። መንግሥት በፈለገው ጊዜ፤ በፈለገው ግምት ተከራዩን ሊያባርረው ይችላል።

የመንግሥት የመሬት ባለቤትነት ማለት፤ ህዝቡን ንብረት ነፍጎ ረግጦ በመያዝ፤ ሹማምንትና ደጋፊዎቻቸው ራሳቸውን የሚያከበሩበት መንገድ ማለት ነው። ስለዚህ፤ ከእንግዲህ ወዲያ መሬት ከመንግሥት ሞኖፖሊ ተላቆ ለህዝቡ በፍህታዊ መንገድ በባለቤትነት እንዲከፋፈል ከስምምነት መድረስ እጅግ አስፈላጊ ነው።

በመጨረሻም፤ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ የተነፈገችው የዲሞክራሲ ሽግግር በአሁኑ ወቅት ሊሳካ የሚችለው በልጆችዋ ቀና መንፈስና ትብብር ብቻ መሆኑን መገንዘብ ያሻል። የውጭ ሀይሎች ኢትዮጵያን ወደዲሞክራሲ ያሸጋግራሉ ብሎ መጠበቅ ካለፈው ታሪክ አለመማርና ኃላፊነትንም አለማክበር ይሆናል።