ዶ/ር ዳንኤል ተፈራ

የኢኮኖሚክስ ኤመረተስ ፕሮፌሰር

ከ6/23/19 እስከ 6/30/19  ባለው ጊዜ ውስጥ ለቤተሰብ ጉዳይ ኢትዮጵያ ውስጥ ነበርኩ። ለመጨረሻ ጌዜ ወደ ኢትዮጵያ የሄድከት የዛሬ ሦስት ዓመት ነበር። ያንጊዜ ያላየሁትን በአሁኑ ቆይታዬ ለማየት ችያለሁ። ፍርሀት ተወግዶ፤ ሰው አንገቱን ሳይደፋ መሄድ፤ እንዲሁም መናገር ችሏል። ከዚህ ቀደም በፊቱ ላይ ይታይ የነበረው ጭንቀት ቀርቶ ዛሬ ፈገግታ ይነበብታል።

ጉዞዬን የጀመርኩት በ6/22/19 ከምኖርበት ከማድስን፤ ውስካንስን ነበር። በፍራንክፈርት አድርጌ በ6/23/19 ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ተኩል ገደማ አዲስ አበባ ገባሁ። ቪዛ ወደሚመታበት ቦታ ስሄድ፤ ስፍራው እንደተለመደው ተራን በማያከብሩ መንገደኞች ተጨናንቋል። የአገልግሎት መስኮቶች ተዘጋጅተው ወጣት ሠራተኞች በኮምፒውተር እየተረዱ የሚቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ይጥራሉ። ተቆጣጣሪው ሥራውን ያፋጠነ መስሎት ተጨማሪ መስኮቶች ከፈተ። ይሁንና ግፊያው ግን አላቋረጠም። ይልቁንም መንገደኞቹ ተራቸውን ካልጠበቁ አገልግሎት እንደማይይሰጣቸ ማስጠንቀቅ ነበረበት።

ተራ ደርሶኝ ቪዛዬን ሳስመታ ወደእኩለለሊት ገደማ ሆነ። እዚያው አውሮፕላን ጣቢያ ከሚገኘው አንድ ባንክ ቆም ብዬ ገንዘብ ከመነዘርኩ በኋላ፤ ሻንጣዬን ፍለጋ ሄድኩ። ለካስ ማድሰን ላይ በተደረገ ስህተት፤ ሻንጣዬ ከኔ ጋር አልመጣም ነበር። ሻንጣዬ በሚቀጥለው አውሮፕላን ይመጣል ስለተባልኩ፤ በእጄ ላይ የያዝኩትን ቦርሳ ብቻ ይዤ ወደ ሆቴሌ ማምራት ግድ ሆነብኝ። የሆቴሉ ለመዚን ነጂ በትህትና ተቀብሎኝ ጉዟችንን ቀጠልን። ስለጉዞዬ እየተነጋገርን ሳለን፤ ”በሀገራችን ትላንት ስለተፈጠረው ነገር ሰምተዋል እንዴ?“ ብሎ ጠየቀኝ። ዜናውን ገና ፍራንክፈርት ላይ ሳለሁ መስማቴን ነግሬው ሁለታችንም ለጉዳዩ እንግዳ በመሆናችን ብዙም ሳናወራ ከሆቴሉ ደርስን ወደተያዘልኝ ክፍል አመራሁ።

በማግስቱም ከሆቴሉ ውስጥ ከምትገኝ የሞባይል ስልክ ሱቅ ሄጄ ሲን ካርድ ገዛሁ። ሱቁ የሚመራው ሙያቸውን ጠንቅቀው በሚያውቁ በሁሉት ወጣት ሴቶች ነበር። እነርሱም ካርዱን ስልኬ ውስጥ ካስገቡ በኋላ፤ የሰጡኝን የሀገር ውስጥ ቁጥር በጥንቃቄ እንድይዝ ነግረው በትህትና ሸኙኝ። ወዲያውኑ ወደአየር መንገዱ መሥሪያ ቤት ደውዬ ሻንጣዬ አለመምጣቱ ተነግሮኝ፤ ሰኞ እለት ሊመጣ ይችላል የሚል ቃል ተሰጠኝ። የመጣሁበት የቤተሰብ ጉዳይ ወደሻሸመኔ የሚያስኬደኝ ቢሆንም፤ በአዲስ አበባም ተመሳሳይ ጉዳዮች ነበሩኝ። ስለዚህ፤ ሻንጣዬ እስኪገኝ ድረስ በአዲስ አበባ የሚጠብቀኝን ጉዳይ ማከናወን ጀመርኩ። በሆቴሉ አማካኝነት ያገኘሁት ባለታክሲ ቅን ሰው ሰለነበር ወደፈለግሁበት ቦታ ለመሄድ ችግር አልገጠመኝም። በቀላሉ ስለተግባባን፤ ደንበኛዬ አደረግሁት። ባለታክሲዎች ብዡ ነገሮችን ይገነዘባሉና አንዳንድ ነገሮችን እጠይቀው ጀመር።

ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ አዳዲስ ታክሲዎች መንገዱን ሞልተውታል። የኔም ደንበኛ የያዘው አዲስ ታክሲ ነበር። ፊት በመጣሁ ጊዜ ታክሲዎቹ በብዛት የወዳደቁ ነበሩ። ስለዚህ፤ ይህ መሻሻል እንደምን ተገኘ? ብዬ ደንበኛዬን ጠየቅሁት። “ይህን ታክሲ ልገዛ የቻልኩት ከጓደኞቼ ጋር ሆነን በማህበር ተደራጅተን ነው። እያንዳንዱን ታክሲ፤ ከቀረጥ ነፃ በ380,000 ብር ነው የገዛነው። ገንዘቡን ያገኘነው ሊብሬአችንን አስይዘን ከባንክ ተበድረን ሲሆን፤ በየወሩ እያንዳንዳችን ዘጠኝ ሺህ ብር እንከፍላለን። ታክሲዋ የምትመጣው ከቻይና ሲሆን ስሟ ሊፋን ይባላል። እኛ ደግሞ፤ ሊፋን የውበት እስረኛ ነው የምንላት፤ እዳዋ ተከፍሎ ስላላለቀ። ያረጀችው ላዳ ደግሞ የልማት ተነሺ ተብላለች” በማለት እያሳቀ አጫወተኝ።

አዲስ አበባ የገባሁት እሁድ ማታ ሲሆን፤ ሻንጣዬን ስጠብቅ ማክሰኞ ደረሰ። ስለዚህ፤ የመለወጫ ልብስ ፍለጋ ወደቦሌ ከታክሲ ደንበኛዬ ጋር አብረን ሄድን። የኢንተርኔት አገልግሎት ስለተቋረጠ፤ ክሬዲት ካርድ መጠቀም አልቻልኩም ነበር። በኪሴ ውስጥ የያዝኩትን ጥሬ ገንዘብ ማብቃቃት ነበረብኝ። ሁለት ዘመናዊ ሱቆች ውስጥ ቆም ብዬ ጥቂት የሚያስፈልጉኝን ነገሮች ገዛሁ። ባለቤቶቹ በወጣትነት ዕድሜ ውስጥ ያሉ፤ የንግድን ሥራ ከትህትና ጋር  አቀላጥፈው የሚያውቁ ነበሩ። በሱቆቹ ውስጥም ይሁን በውጪ ምንም የገጠመኝ ችግር አልነበረም። አሜሪካን ሳለሁ የሰማሁት ግን ስለኪስ አውላቂ መበርከት የፈጠራ ወሬ ነበር። ሸመታዬን እንዳገባደድኩ ስልክ ተደወለልኝ። “ሻንጣህ መጥቷልና መጥተህ መውሰድ ትችላለህ” የሚል ነበር። ከደንበኛዬ ጋር ተያይዘን ወደቦሌ አመራን። አውሮፕላን ጣቢያ እንደደረስን፤ ደንበኛዬ ከአጥር ውጪ ሆኖ መጠበቅ ነበረበት። እኔ ውስጥ ገብቼ ሻንጣዬን ይዤ ወጣሁ። ሻንጣዬን እየጎተትኩ ከዋናው በር ስደር፤ ሁለት የፌደራል ፖሊስ የሚሏቸው በሲዳምኛ ቋንቋ ሲነጋገሩ ሰምቼ፤ “እንደምን አላችሁ? የሀገሬ ሰዎች” አልኳቸው። እነርሱም፤ በፈገግታ፤ ከኔ ጋር ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ በትህትና ሸኙኝ።   ይህ ሁሉ ሲሆን ደንበኛዬ በርቀት ሆኖ ያይ ነበርና፤ ሻንጣዬን እየጎተትኩ ከአጠገቡ ስደርስ፤ ”ፌደራሎቹ ሲያነጋግሮት ሰግቼ ነበር። ነገር ግን ትሳሳቃላችሁ“ አለ። የሀገሬ ሰዎች መሆናችውን ነግሬው፤ በማገስቱ እሮብ ዕለት ወደሻሸመኔ መሄድ ስለነበረብኝ፤ ቲኬት ለመግዛት ወደአውቶቡስ ጣቢያ ሄድን።ለእኔና አብራኝ ለምትሄደው የቤተዘመድ ልጅ ሁለት ቲኬቶች፤ ስላም ከሚባል አውቶቢስ ቢሮ ገዝቼ፤ ደንበኛዬ ከሆቴሌ አድርሶኝ ሄደ።

አውቶቡሱ ከመስቀል አደባባይ የሚነሳው ከቀኑ ስድስት ሰዓት መሆኑ ስለተነገረን፤ ቀደም በለን ከስፍራው ደረስን። ከውጪ ሲታዩ የተደረደሩት አውቶቡሶች አሜሪካን ያየኋቸውን መጸዳጃ ያላቸው ዘመናዊ አውቶቡሶች ይመስላሉ። እነዚህ ግን መጸዳጃ የሌላቸው ቻይና የሚሠራቸው አውቶቡሶች ናቸው። ሁኔታው ስላሳሰበኝ፤ የአውቶቡሱን አሳፋሪ “አውቶቡሱ ለእረፍት መንገዳችን ላይ ይቆማል ወይ?“ ብዬ ጠየቅሁት። ”አዎን አባት፤ ምንም ቸግር የለም“ አለኝ። ለማንኛውም፤ ከአሁኑ ፊኛዬን መገላገል ይሻላል ብዬ አንደኛውን ረዳት አሳፋሪ በአካባቢው መጸዳጃ ቤት እንዳለ ጠየቅሁት። ከመንገዱ ባሻገር ካለው ቡና ቤት ውስጥ ያለውን መጸዳጃ ቤት መጠቀም እንደሚቻል ነገረኝ። ለመሞት ካልሆነ በስተቀር፤ መስቀል አደባባይ ላይ መንገድ ማቋረጥ የሚሞከር አይደለም። ጭንቀቴን የተመለከተው ረዳት አሳፋሪ ከለላዬ በመሆን እንደየአራት ዓመት ልጅ እጄን ይዞ አሻግሮ መልሶ አመጣኝ። የአዲስ አበባ መኪና ነጂዎች የትራፊክ ህግና መንገደኛውን እንዲያከብሩ ከተፈለገ፤ ሲያጠፉ ጥብቅ የገንዘብ መቀጫ ሊጣልባቸው ይገባል።

ወደአውቶቡሱ ተመልሼ ወንበሬን እንደያዝኩ፤ አውቶቡሱ መንቀሳቅስ ጀመረ። እስከአዳማና ሞጆ መገንጠያ ድረስ መንገዱ ዘመናዊ ነው። አውቶቡሱ ሞጆን ተከትሎ ወደሀዋሳ አመራ። ወዲያውኑ ለፍተሻ እንዲቆም ተደረጎ ሁላችንም ከአውቶቡሱ ወረድን። ፍተሻው ለምን እንዳስፈለገ ሹፌሩን ብጠይቀው፤ በሰሞኑ በጀነራሉ መገደል ምክያት የተጠረጠሩ ሰዎች እንዳያመልጡ በሚል ስጋት ነው አለኝ። ሁላችንም ከፍተሻው በኋላ አውቶቡሱ ውስጥ ገብተን ጉዞአችንን እንደገና ቀጠልን። ለሚቀጥሉት ሦሰት ሰዓቶች ከተጓዝን በኋላ፤ መቂ ወይም ዝዋይ ላይ ለእረፍት እንቆማለን የሚል ግምት ነበረኝ። ነገር ግን፤ አውቶቡሱ ዝዋይን ካለፈ በኋላ ቁጥቋጦ ያለበት ሜዴማ ቦታ አጠገብ አቆመ። የሹፌሩ ረዳት የውሀውን ሰም ደጋግሞ እየጠራ “ውረዱ፤ ውረዱ” አለ። እኔም ከአውቶቡሱ ወርጄ መጸዳጃ ቤት ያለ መስሎኝ ወደኮረብታው ሳመራ፤ ሹፌሩ እዮረጠ መጥቶ፤ “ኮረብታው ሴቶቹ እንደሽፋን የሚጠቀሙበት ነው፤ ወንዶች ሜዳውን ነው የሚጠቀሙት” አለኝ። የረሳሁትን ልማድ አሁን ላድርግህ ብለው እሺ እንደማይለኝ ሰለማውቅ ተመልሼ አውቶቡሱ ውስጥ ገባሁ። ወንበሬ ላያ ቁጭ ካልኩ በኋላ ነገሩ ይከነክነኝ ጀመር። ወትሮ ከልጅነቴ ጀምሮ እንደማውቀው ከሆነ፤ አውቶቡስ የሚቆመው ሆቴሎች ያሉበት ከተማ ውስጥ ነው። ቁጥቋጦ ያለበት ፈልጎ የመቆም ኋላቀርነት ከየት መጣ?። ሀገር ወደፊት እንጂ ወደኋላ እንዴት ይሄዳል?። ሀገሪቱን የገጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳይሆን የሥልጣኔ እጥረት ነው። ለምሳሌ፤ በእየሀምሳ ኪሎሜትሩ መጸዳጃ ቤት ቢሠራ፤ ተሳፋሪዎች ትንሽ ገንዘብ በእርዳታ መልክ እየሰጡ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። የሚሰበሰበው ገንዘብ ሠራተኛ ተቀጥሮበት መጸዳጃ ቤቱ በንጽህና እንዲጠበቅ ይደረጋል። በሀገሪቱ ሥልጣኔ ቢኖር ኖሮ፤ አስራሦስት ወራት ሙሉ ፀሐይ ባለበት ሀገር መብራት በየጊዜው ባልተቋረጠም ነበር።

ወደአስራአንድ ሰዓት ገደማ እኛን ሻሸመኔ ላይ አውርዶ፤ አውቶቡሱ ጉዞውን ወደሀዋሳ ቀጠለ። ሻሸመኔ የሄድኩት በጣም የምንወደው አጎታችን ከዚህ ዓለም በሞት ስለተለየን እርሜን ለማውጣት ነበር። ሻሸመኔ ከማደግዋ በላይ በባጃጅ ብዛት የተጨናነቀች ከተማ ሆናለች። ወደአጎቴ ቤት ከመሄዳችን በፊት ሆቴል ለእኔ መያዝ ስለነበረብኝ ባጃጅ ተከራይተን ሆቴል ፍለጋ ጀመርን። ከጥቂት ፍለጋ በኋላ ከከተማው ትንሽ ወጣ ብሎ ሀዋሳ መንገድ ላይ አንድ ሆቴል አገኘን። አብራኝ የመጣችው የቤተዘመዳችን ልጅ አጎታችን ቤት ስለምታድር፤ ለእኔ በቀን ስድስት መቶ ብር ከፍዬ አንድ ክፍል ያዝኩና ወደአጎታችን ቤት አመራን። እሮብ ማታውንና ሐሙስን ከቤተሰብ ጋር አሳለፍኩ። ቅዳሜ ዕለት ወደአዲስ አበባ ጊዜ ለመቆጠብ በአውሮፕላን ከሀዋሳ መመለስ ስላለብኝ፤ ቲኬት ለመግዛት አርብ እለት ከአጎቴ ቤት ልጆች አንዳቸውን ይዤ በሚኒቫን ወደሀዋሳ መሄድ ነበረብኝ። ከሻሸመኔ ሀዋሳ ከሀያ አምስት ኪሎሜትር አይበልጥም። ከከተማው ወጣ ብለን ጥቁር ውሀ ልንደርስ ስንል፤ ትንሽ ከመንገዱ ራቅ ብሎ በስተቀኝ በኩል ብዙ የቆርቆሮ ቤቶች አይቼ ምን እንደሆኑ አጠገቤ የተቀመጠውን ተሳፋሪ ጠይቅሁት። “ከሶማሌ የተፈናቀሉ ሦስት ሺህ የሚሆኑ የኦሮ ቤተሰቦች መኖሪያ ነው” አለኝ። በአካባቢው ምንም ዓይነት ኢኮኖሚ አይታይም። የሚኖሩት በመንግሥት እርዳታ  መሆኑንም ተረዳሁ።

ጥቁር ውሀ ስንደርስ ለፍተሻ ቆምን። ፈታሾቹ የደቡብ ፖሊሶች የሚባሉት ናቸው። ምንም ንግግር የለም፤ የመኪናውን በር መበርገድ ብቻ ነው። በሩን እንዲያ ሲበረግደው ባልጠነቀቅ ኖሮ፤ መንገዱ ላይ እዘረገፍ ነበር። ከፍተሻው በኋላ ሀዋሳ ገብተን አውቶቡስ ጣቢያው ላይ ወረድንና የብዙ ጊዜ ባለውለታ ዘመዴን ለመገናኘት ባጃጅ ይዘን ወደሱቁ አመራን። ከዘመዴ ጋር ከተገናኘን በኋላ በርሱ መኪና ሆነን የአይሮፕላን ቲኬቴን ገዝቼ ሆቴል ፍለጋ ጀመርን። አርብን ሀዋሳ አድሬ፤ ቅዳሜ ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ መብረር ነበረብኝ። አንድ ሀይቁ ዳር ወዳለ ሆቴል ስናመራ ወደሆቴሉ የሚያስገባው መንገድ ላይ፤ ወጣቶች ፍተሻ ያካሄዳሉ። ፖሊሶችም አሉ። ፍተሻውን የሚያካሄዱት ግን ወጣቶቹ ናቸው። መኪናችን ከቆመበት ቦታ አንደኛው በኔ በኩል መጥቶ እንደተለመደው በሩን ከፈተው። ብትጠይቀኝ ኖሮ እኔው እከፍትልህ ነበር አልኩት። ምንም መልስ የለም። አለቃቸው  ወደመኪናችን ሲመጣ ዘመዴን አስታውሶት ኖሮ “ጋሼ እገሌ ሰላም ነው?” ሲል ጠየቀ። ቀጥሎም፤ “ለሁላችንም ጥቅም ነው ፍተሻ የምናደርገው” አለ። እኔም ፖሊሶቹ ቆመው ወጣቶቹ ለምን እንደሚፈትሹ ስላልገባኝ፤ “እናንተ ማን ናችሁ?” ብዬ ጠየቅሁት። “እኛ  እጄቶ ነን” አለ። ወዲያውኑ እስከአፍንጫቸው የታጠቁ ወታደሮች ፒካፕ መኪናቸውን አጠገባችን  ቆም አደረጉ። ከመካከላቸው አንደኛው አንገቱን ወጣ አድርጎ “ጋሼ እገሌ፤ ሰላም ነው?“ አለ። ፍተሻው አልቆ ሆቴሉ በር ላይ ሰንደርስ ከበስተግራችን በማጉያ የሚረዳ ድምፅ ሰማን። የሆቴሉ ዘበኛ በነገረን መሠረት ከእጄቶ ስብሰባ የሚመጣ ድምፅ ነበር። ማደራዬን ከያዝኩ በኋለ የዘመዴን ልጅ ጨምረን ሦስት ሆነን ምሳችንን በልተን አብረን ጥሩ ጊዜ አሳለፍን።  የአጎቴን ቤተሰብ መሰናበት ስለነበረብኝ የዘመዴ ልጅ ጓደኛ በራሱ መኪና ሻሸመኔ አድርሶ ስለመለሰኝ ባለትልቅ ውለታዬ ነው።

የዘመዴ ልጅ ጓደኛ፤ ሀዋሳ ውስጥ በንግድ ሥራ  ተሰማርቶ የሚኖር፤ ባለትዳር፤ የሁለት ልጆች አባት ነው። ከሻሸመኔ  ወደ ሆቴሌ ካመጣኝ በኋላ፤ ሀይቁ አጠገብ አንድ ጠረጴዛ ይዘን ስለአንዳንድ ጉዳዮች በሰፊው ተወያየን። ዋነኛው የተወያየንበት ጉዳይ ስለሲዳማ የክልል ጥያቄ ነበር። ጥያቄውን ከሚደግፉና ከማይደግፉ ሰዎች የተጋነኑ አስተሳሰቦች ይሰማሉ። የርሱ አስተሳሰብ ከዚህ ለየት ይላል። እኔም በአቋሙ እስማማለሁ። ሲዳማ ክልልን አልፈጠረም። ሌሎቹ ጥቅማቸውን የሚያስከብሩት ክልል ስላላቸው ሰለሆነ፤ እኛም ክልል ይገባናል ነው ጥያቄው። በነገራችን ላይ፤ ጥያቄው ወደ ሌሎቹም መዛመቱ የማይቀር ነው። ክልል የፓለቲከኞችን ኪስ ያዳብር እንደሆን እንጂ፤ ህዝቡን አይጠቅምም። ሰው ከሰው ተምሮ ነው የሚበለፅገው። ቋንቋና ህዝብ አንድ ናቸው። ካልተደባለቁ ይጠፋሉ። አሜሪካንም ሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ፤ አንዳንድ ሰዎች “ለውጡን እንዴት አየኸው?” በማለት ጠይቀውኛል። የዛሬ ሦስት ዓመት ካየሁት ጋር ሲነጻጸር፤ የማየው የተስፋ ጭላንጭ እንጂ ለውጥ አይደለም። የክልል ሥርአት ተወግዶ መሬት የግል ንብረት እስካልሆነ ድረስ እውነተኛ እድገት የሚያመጣ ለውጥ ሊኖር አይችልም። ክልል፤ እኩል ዜግነትን በመንፈግ ብዙ ህዝብ በግፍ አፈናቅሏል። ሰዉ ዜግነቱን ተነፍጎ ከሚኖር መሰደድን ይመርጣል። ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብትና ጥሩ ህዝብ ያላት ሀገር ናት። ቅዳሜ ዕለት ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ ስበር ከሰማይ ሆኜ የተመለከትኩት የተፈጥሮ ውበት ከአእምሮዬ የማይጠፋ ነው። በማግስቱም የኢትዮጵያን ምድር የለቀቅሁት በሀገሪቱ ያየሁት የተስፋ ጭላንጭል እንዳይጠፋ እየጸለይኩ ነበር።