ከዶ/ር ዳንኤል ተፈራ
የኢኮኖሚክስ ኤመረተስ ፕሮፌሰር

የክልል ሥርአት ከተመሠረተ ሀያስምንተኛ ዓመቱን ይዟል። ክልልን በዋነኛነት የመሠረተው ሀገሪቱን በመሣሪያ ኃይል የተቆጣጠረው ሕወሓት ነው። የክልል ሥርአት፤ ስሙ እንደሚያመለክተው ሁሉ፤ የመሬት ክፍፍል ሥርአት ነው። የሁሉንም መብት በእኩልነት የማስከበሪያ አደረጃጀት አይደለም። ስለዚህ፤ በተለያዩ ቦታዎች በሕይወትና በንብረት ላይ ብዙ ጉዳቶች ደርሰዋል። እየደረሱም ነው።

ለምሳሌ፤ በቅርቡ በባሕር ዳር የተፈጠረውን የሕይወት መጥፋት ከዚህ ነጥሎ ማየት አይቻልም። ሕወሓት፤ ከጎንደርና ከወሎ መሬት ወስዶ ወደትግሬ ግዛት በመከለሉ፤ በቀላሉ ሊጠፋ የማይችል እሳት አስነስቷል። ስለዚህ ነው ክልል የመብት እኩልነት ሥርአት አይደለም ያልኩት። የመሬት ነጠቃና የግዛት መስፋፋት ነው ቢባል ያዋጣል። ስለዚህ፤ ክልል ኋላቀር አስተሳሰብ ነው። ምክንያቱም፤ በጉልበት ከሚያመርቱት የሀብት መጠን ይልቅ፤ በሰላም የሚያመርቱት የሀብት መጠን ይበልጣል።

የክልል ሥርአት ሁለት ዓይነት ጥያቄዎች አስነስቷል። አንደኛው፤ “የተነጠቁ መሬቶቻችን ይመለሱልን” የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ “ክልል እንሁን” የሚል ነው። የዚህ ጽሑፍ ትኩረት በሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ ላይ ነው። አላማው የሲዳማን ክልል የመሆን ጥያቄ ለመደገፍ ወይም ለመንቀፍ አይደለም። ስለክልል ሥርአት ያለኝን አስተሳሰብ  አስቀድሜ ከዚህ በላይ ገልጫለሁ።

ለማስታወስ ያህል፤ ተወልጄ ያደግሁት በይርጋ ዓለም ከተማ በሲዳማ አውራጃ ግዛት (አሁን “ዞን” በሚሉት) ነው። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩንቨርሲቲ በምማርበት ጊዜ፤ የአስተማሪነት አገልግሎት ለመስጠት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን በይርጋ ዓለም ራስ ደስታ ት/ቤት (የቀድሞ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቴ) አስተምሬአለሁ። ብዙውን አድሜዬን ያሳለፍኩት በወጪ ሀገር ቢሆንም፤ የሲዳምኛ ቋንቋ ጨርሶ አልጠፋኝም። ስለዚህ፤ ሲዳማን ከሞላ ጎደል ሳላውቀው አልቀርም። የሲዳማን ወረዳ ግዛቶች፤ በተለይ አለታ ወንዶንና ሀዋሳን በደንብ አውቃቸዋለሁ። ሀዋሳን የማውቀው ገና ከተማው ሳይቆረቆር ነው። ቦይስካውት በነበርንበት ጊዜ፤ ከይርጋ ዓለም ወደሀዋሳ እየሄድን ድንኳን ተክለን ቅዳሜና እሁድን እናድር ነበር።

ሲዳማ፤ እንደብዙዎቹ የኢትዮጵያ ስፍራዎች፤ በተፈጥሮ ሀብትና ውበት የታደለ ሀገር ነው። መሬቱ ቡና፤ እንሰት፤ በቆሎ፤ ገብስ፤ ጥራጥሬ፤ የሸንኮራአገዳ፤ የስር እህሎች (ድንች፤ የስኳር ድንች፤ ቦይና፤ ቆልጮማ)፤ አደንጓሬ፤ ቦሎቄ፤ የዱባ ዓይነቶች፤ ቃሪያና ሚጥሚጣ፤ ልዩልዩ ሽንኩርቶችና ጎመኖች እንዲሁም የተለያዩ ፍራፍሬዎች ይበቅሉበታል። የወተትና የስጋ ከብቶች እንዲሁም የጭነት ከብቶች ይረቡበታል። ረጃጅም ወንዞችን፤ ለም ሸለቆዎችን፤ ፈዋሽ ፍልውሀዎችን እንዲሁም የተንጣለለውን የሀዋሳን ሀይቅ ያካትታል።

የሲዳማ ህዝብ በታሪኩ ሰላም ወዳድ ነው። እንግዳ ተቀባይነቱ በአመክሮ ይነገርለታል። አብረን እንብላ (አሞ ኢንቶ) የሚል ባህል ነው የነበረው። ከቅርብ ጊዜና ከሰሞኑም የታየው፤ የሲዳማ ወጣቶች በመካከላቸው ሠርቶ የሚኖረውን ህዝብ ንብረት ማጥፋትና ነዋሪውንም መጉዳት ጥንታዊው የሲዳማ ባህል ሳይሆን፤ የክልል ሥርአት የፈጠረው አዲስ ባህሪ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ጠባይ ለጊዜው የሲዳማ ፖለቲከኞችን የሚጠቅም ቢመስልም፤ ነጋዴውንና የተቀረውን ሙያተኛ ክፍል ከሀገር ስለሚያባርር የማታ ማታ መልሶ የሚጎዳው ሲዳማን ነው።

በተጨማሪም፤ እንዲህ ዓይነቱ ጭካኔ የታከለበት ድርጊት ከውስጥም ሆነ ከውጪ ሀገር፤ ለተጠየቀው የሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ፤ የፖለቲካ ድጋፍ ሊያስገኝ አይችልም። በሌላ በኩል፤ የሀገሪቱ ገዢዎች የሲዳማን ክልል የመሆን ጥያቄ በሰበብ ባስባቡ መጎተት፤ የተፈጠረውን ችግር ያባብሰዋል እንጂ አያስወግደውም። ለምሳሌ፤ ሕወሓትና ኦነጎ ሕዝበ-ውሳኔ ሳይጠየቁ በኃይላቸው ነው ክልሎቻቸውን የመሠረቱት። ስለዚህ፤ ሲዳማና የተቀሩትም የደቡብ ህዝቦች እየተባሉ የሚጠሩት፤ ክልል የመሆን ጥያቄአቸው ካልተፈቀደ፤ ጊዜ ጠብቀው ጠመንጃ ማንሳታቸው የማይቀር ነው።

በአንድ በኩል፤ “የተወሰዱብን መሬቶች ይመለሱልን”፤ በሌላ በኩል ደግሞ፤ “ክልል መሆን እንፈልጋለን” የሚሉት ሁለት ጥያቄዎች፤ ማቆሚያ የሌለውን የክልል ሥርአትን የተፈጥሮ ጉድለት ነው የሚያሳዩት። የክልሎች ቁጥር ጨመረም፤ ቀነሰም፤ የክልል ሥርአት ጨርሶ እስካልተወገደ ድረስ በሀገሪቱ ውስጥ ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና ሊኖር አይችልም። እውነቱ ይህ ከሆነ ዘንድ፤ ኢትዮጵያ “ወደዬት እያመራች ነው?“ የሚለውን ጥያቄ መጠየቁ ተገቢ ይሆናል። መልሱም፤ “ወደተፈጥሮ ታሪኳ” የሚል ነው።

ኢትዮጵያ ብዙ ቋንቋዎች የሚነገሩባት ሀገር በመሆንዋ፤ እያንዳንዱ የቋንቋ ክፍል የሰፈረው በአነስተኛ መሬት ላይ ነው። ስለዚህ የሀገሪቱ የቋንቋ ክፍሎች እያንዳንዳቸው እንደሀገር እራሳቸውን  ችለው መኖር አይችሉም። ስለዚህ፤ ወደዱም፤ ጠሉም፤ አብረው እንዲኖሩ የተፈጥሮ ታሪካቸው ያስገድዳቸዋል። ያለበለዚያ ይጠፋፋሉ። የቀድሞው የክፍለሀገር አወቃቀር በሰላም እንዲኖሩ አድርጓል፤ ምንም እንኳን ፌደራላዊ ባይሆን። የኢትዮጵያ የቋንቋ ክፍሎች በአንድ ላይ ኖረው ችግሮቻቸውን መፍታት ካልቻሉ፤ ስለተከፋፈሉ ችግሮቻቸውን ያስወግዳሉ ማለት አይደለም። ችግሮቻቸውን ሊፈቱ የሚችሉት፤ የእያንዳንዳቸውን ራስን በራስ የማስተዳደር ፌደራላዊ መብት አክብረው፤ ዲሞክራሲያዊ አንድነትን በመፍጠር፤ የሰው ልጅ ሁሉ መብት በእኩልነት የሚከበርባት አንድ ኢትዮጵያን ሲመሠርቱ ብቻ ነው።