ዶ/ር ዳንኤል ተፈራ

የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር፤ ኤመረተስ

ከጥምቀት የቃናዘገሊላ በዓል ጀምሮ፤ በወልድያ፤ ቆቦ፤ መርሳና ሲሪንቃ ህዝባዊ እምቢተኝነት መቀስቀሱን የተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች ዘግበዋል። ከዚያም ጋር በተያያዙ ግጭቶች፤ ሕይወትና ንብረት መጥፋቱን እነዚሁ ድርጅቶች አስታውቀዋል።

በዜና አቅራቢዎቹ ዘገባ መሠረት፤ የሕወሀት መንግሥት በወሰደው ወታደራዊ እርምጃ፤ ከአስራ አምስት የማያንሱ ሰዎች፤ በተለይ ወጣቶች፤ የአስራሦስት ዓመት ልጅ ጨምሮ፤ ተገድለዋል። ብዙ ስዎች ቆስለዋል፤ ታስረዋል፤ በመታደንም ላይ ናቸው።

በተጨማሪም፤ “የአማራ ክልል” ፕሬዝዳንት፤ የግጭቱ ዋና መነሻ የተጠራቀመ የህዝብ ችግር ነው ማለታቸውንና የወታደር ሃይል ወደስፍራው መግባቱን አለመደገፋቸውን ገልጸዋል። እንዲሁም፤ የሃይል አዛዡ “የወታደሩ ዓላማ የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለመከላከል ነው” ማለታቸውን ጠቅሰዋል።

ያም ሆነ ይህ፤ ለተፈጠረው ችግር መፍትሄው ባልታጠቀ ህዝብ ላይ መዝመት አይደለም። ላለፉት 26 ዓመታት ለተፈጠረው ከፍያለ የህይወትና የንብረት ጥፋት ዋና ምክንያት የሆነውን በዘር የተከፋፈለ አገዛዝ ማሰወገድ ነው መፍትሄው። የዘር አገዛዝ ከመምጣቱ በፊት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ፤ እንደተቀረው አፍሪካ ሳይሆን፤ በእርስ በርስ ግጭት የታወቀ አይደለም።

የዘር አገዛዝ፤ የሕወሀት ገዢዎች ለጥቅማቸው ሲሉ በህዝቡ ላይ በራሳቸው ሃይል የጫኑት ዘዴ ነው። በእነርሱ አስተሳሰብ፤ ሃይል መብት ነው። ስለዚህ፤ “አሸንፈናል፤ በደማችን ያገኘነው ነው፤” በማለት  አገሪቱን በዘር ከፋፍለው ራሳቸውንና ደጋፊዎቻቸውን ማበልጸጋቸው ይታወቃል።

የተቀረው ህዝብ ግን “አገሬን ተቀማሁ፤ መሬቴን ተነጠቅሁ፤ ቤቴ ፈረሰብኝ፤ በገዛ አገሬ ሠርቼ መብላት ተከለከልኩ፤ የምበላው አጣሁ” እያለ ሲጮህ፤ ችግሩን የሚሰማለት መንግሥት የለም። ችግሩ፤ እራሱ መንግሥት የተባለው ነው። ህዝቡ ብሶቱን  ለማሰማት ከተሰለፈ፤ የሚጠብቁት መከራዎች እንደ የዱላ ውርጅብኝ፤ ተደብቆ-ተኳሽና እስር ቤት መታጎር ያሉት ናቸው።

የሕወሀት ገዢዎች የዘረጉት የስስት አገዛዝ፤ ውሎ አድሮ ሊቋቋሙት የማይችሉትን ህዝባዊ እምቢተኝነት ቀስቅሶባቸዋል። “ወያኔ አይገዛንም፤ እራሳችንን እናስተዳድራለን፤ አንድነታችንን እንፈልጋለን” እያለ የሰሜን ወሎ ህዝብ በቆራጥነት እምቢተኝነቱን ገልጿል። ከዚህ በፊት፤ በኦሮሞ ክፍለሀገሮችና በጎንደር የተስተጋባውም ይኸው ነበር።

የሕወሀት ገዢዎች በየጊዜው የሚወስዱት ጭካኔ የተመላበት ወታደራዊ እርምጃ፤ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ እምቢተኝነት ያባብሰዋል እንጂ አያበርደውም። በህዝባዊ እምቢተኝነት፤ በብዛት ተሳታፊው አዲሱ ትውልድ በመሆኑ፤ ችግሩ በወታደራዊ ሃይል ሊገታ አይችልም።

አዲሱ ትውልድ፤ በሠለጠነው ዓለም ስለአለው የሰው ልጅ ነፃነትና እኩልነት በመገናኛ መንገዶች  ይከታተላል። ያን የሚያየውን ጸጋ ለራሱ እንዲሆንለትም ይመኛል። የሰው ልጅ፤ በቀለም ወይም በዘር ቢለያይም፤ በፍላጎቱ ግን አይለያይም።

የሕወሀት ዘርተኮር አገዛዝ ወገንተኛ በመሆኑ፤ የሰው ልጅ ተመሳሳይ ፍላጎት ይኑረው አይኑረው ደንታው አይደለም። ለራሱና ለተከታዩቹ የሚሰጠውን መብቶች ሌላውን ይነፍጋል። ሌላው፤ ይህን መድሎ ዝም ብሎ ለዘላለም አይመለከትም። ስለዚህ፤ በሕወሀት ገዢዎችና በህዝቡ፤ በተለይ በወጣቱ ትውልድ፤ መካከል በየጊዜው ግጭት መፈጠሩ የማይቀር ነው።

የሕወሀት ገዢዎች፤ ሌላውን አግለው የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚያስከብሩበትን የዘርተኮር አገዛዝ  በራሳቸው ፈቃድ አይተውም፤ ካልተገደዱ በስተቀር። ይሁንና፤ ለዚህ መድኃኒቱ ጦርነት ነው ማለት አይደለም።

የሕወሀት ገዢዎች ዘርተኮር አገዛዛቸውን እንዲተውና ከህዝቡ ጋር በእኩልነት፤ እንዲሁም በአንድነት፤ እንዲኖሩ የሚያስገድዳቸው፤ በየክፍለሀገሩ ሊነሳ የሚችለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ብቻ ነው። የዘርተኮር አገዛዝ ከኢትዮጵያ ከጠፋ፤ ሁሉም ሠርቶ እራሱን ለማሻሻል እኩል መብት ይኖረዋል፤ የሀገሪቱም ሀብት ያድጋል።