ዶ/ር ዳንኤል ተፈራ
የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር፤ ኤመረተስ።

ባለፈው ሰሞን፤ የሕወሀት ገዥዎች፤ እንዲህ ብለው ነበር፦ “በተደጋጋሚ የኢኮኖሚ ድል አስመዝግበናል፤ ረሀብ ያገሪቱ መታወቂያ መሆኑ አክትሟል፤ የዲሞክራሲውን ምህዳር እናሰፋዋለን፤ ወዘተ” ይህ ዓይነቱ አነጋገር ከዚህ በፊት ተደጋግሞ ተነግሯል። ምእራባዊ መንግሥታትና “የልማት ድርጅቶችም” ይህንኑ ፖለቲካ ለብዙ ጊዜ ሲያስተጋቡ ቆይተዋል።

ህዝቡ ግን ግራ መጋባቱ ግልጽ ነው። “ተደጋጋሚ የኢኮኖሚ ድል ከተመዘገበ፤ እንዴት ጠግበን መብላት አቃተን?” እያለ ይጠይቃል። ይህ ትክክለኛ ጥያቄ ነው። መልሱ ግን፤ ለመንግሥትና ለውጪ ደጋፊዎቻቸው ስውር አይደለም።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተከታታይ አስመዘገበ የሚባለው እድገት፤ የድንጋይና የአሸዋ እድገት እንጂ የእህል እድገት አይደለም። ህዝቡ፤ “የዘይት ያለህ፤ የስኳር ያለህ” ሲል፤ ኢኮኖሚው ሲሚንቶና ኖራ ያቀርባል። የእድገት ቁጥር ማደግ ትርጉም የለውም፤ ውስጡ ካልተመረመረ።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፤ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ከእጅ-ወደ-አፍ ኢኮኖሚ ስለሆነ መጥፎ ጊዜን መቋቋም አይችልም። ስለዚህ፤ የተፈጥሮ አደጋ በተከሰተ ቁጥር፤ የረሀብ እልቂት ይከተላል ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቱ እልቂት፤ መንግሥታት ሳይቀሩ ህብረተሰቡን ያናጋል። የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን መንግሥት የጣለው፤ የ1966ቱ የወሎ ረሀብ ነው።

ከዚያ በኋላ በተከታታይ የተፈጠረው የትግሬ ረሀብና የውጪ እርዳታ ፖለቲካ፤ ሕወሀት አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር አስችሎታል። እስከዛሬ የአሜሪካን የእህል እርዳታ ባይኖር ኖሮ፤ የሕወሀት ገዥዎችም በተራቸው ገና ድሮ ተሰናብተው ነበር።

ላለፉት 26 ዓመታት፤ አገሪቱን በተለያዩ ቦታዎች በተደጋጋሚ ድርቅ ሲያጠቃት ነበር። ነገር ግን፤ የረሀብ እልቂት ያልተከሰተው፤ ኢትዮጵያ እራስዋን በምግብ ስለቻለች ሳይሆን፤ ካሜሪካን መንግሥት በገፍ በምታገኘው የእህል እርዳታ ነው።

ኢትጵዮጵያ፤ የምግብ ክፍተት ያላት አገር ናት። ይህም ማለት፤ አገሪቱ ከውጪ የምትገዛው የእህል መጠን፤ ወደውጪ ከምትልከው ይበልጣል ማለት ነው። ይህ ክፍተት በየዓመቱ ከአንድ እስከ ሁለት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ይደርሳል። የአሜሪካን የእህል እርዳታ ባይኖር ኖሮ፤ በተደጋጋሚ የረሀብ እልቂት ሊፈጠር ይችል ነበር።

ስለዚህ፤ በየጊዜው የሚነገረው የኢኮኖሚ እድገትም ሆነ የምግብ ዋስትና፤ በማስረጃ የሚደገፍ ሳይሆን፤ ሆን ተብሎ የሕወሀትን ሕገወጥ ገዢነት ለመሸፋፈን የሚደረግ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ነው።
እንድ አገር ወይም ድርጅት ሌላውን ነፃ አገር በመሣሪያ ሀይል ከያዘ፤ ይህ አድራጎት ህገወጥና ቅኝ አገዛዝ ነው የሚባለው። ስለዚህ፤ በ1983 ዓ. ም. ሕወሀት አዲስ አበባን በወታደር ሀይል መያዙ፤ ከዚህ የሚለይ አድራጎት አይደለም።

ለሕወሀት ወታደር፤ በወቅቱ ካሜሪካን መንግሥት የተደረገው የፋይናንስና የዲፕሎማቲክ ሽፋን፤ አሜሪካንን ለድርጊቱ ፈቃድ ሰጪና ተባባሪ ያደርጋል። አንዳንድ ፖለቲከኞች እንደሚሉት ሳይሆን፤ የሕወሀት ወታደር ተሸቀዳድሞ አዲስ አበባን አልያዘም። በአሜሪካን መንግሥት ፈቃድና ትብብር የተደረገ ነው።

ይህ የተዛባ የአሜሪካን መንግሥት ውሳኔ፤ የኢትዮጵያን ወደዲሞክራሲ የመሸጋገር ዕድል አሰናክሏል። ዲሞክራሲ ባሸናፊነት የሚወሰድ ድል አይደለም። ወይም ደግሞ፤ ላሸናፊዎች የሚሰጥ ሽልማት አይደለም።

ዲሞክራሲ ማለት፤ እንደጠላት ወይም ባለንጣ የሚቆጥሩትን ማጥፋት ማለት አይደለም። ዲሞክራሲ ማለት፤ የጠላት ወይም የባላንጣ በነፃነትና እኩልነት መኖር መቻል፤ ለራስም ነፃነትና እኩልነት አስፈሊጊ መሆኑን መገንዘብ ማለት ነው።

በወቅቱ፤ ባሜሪካን የውጪ ጉዳይ አማካሪዎች ስለአሜሪካን ተሳትፎ የተሰጠው ምክንያት፤ “ኢትዮጵያ የጠላት አገር ነች፤ ተጠያቂው የመንግሥቱ ሀይለማሪያም መንግሥት ነው” የሚል ነበር።

ይሁንና፤ የአሜሪካን መንግሥት፤ በቤተእስራኤሎች ጉዳይ ከመንግሥቱ ሃይለማሪያም መንግሥት ጋር ስላልተስማም፤ ባገሩ ውስጥ ላሉ የእስራኤል ጥቅም አስከባሪ ቡድኖች ብቻ ሲል በነፃ ህዝብ ላይ የፈለገውን መንግሥት የመጫን መብት አለው ማለት አይደለም። ይህ አፈጻጸም የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም ከግንዛቤ ያላስገባ ስለነበር፤ ህዝቡ ላለፉት 26 ዓመታት የሕወሀት ተገዢ ሆኖ እንዲኖር አድርጎታል።

ከእንግዲህ፤ በኢትዮጵያ ሰላምና ብልጽግና እንዲሰፍን ከተፈለገ፤ ሕወሀት በገዢነት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ በተገዚነት ሊቀጥሉ አይችሉም። ስለዚህ፤ የተባለው “የየዲሞክራሲ ምህዳር ሊሰፋ” የሚችለው፤ ስለድንጋይ እድገትና ስለሌለው የምግብ ዋስትና በማውራት አይደለም። የሕወሀት ገዥነት ተወግዶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነቱን ሲያገኝ ብቻ ነው።