ዶ/ር ዳንኤል ተፈራ

የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር፤ ኤመረተስ

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር፤ በማርች 10, 2018 ዓ. ም. የገዢው ክፍል ወታደሮች፤ ያለምንም ምክንያት በሞያሌ ከተማ በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ቶክስ በመክፈት ከአስር ሰዎች በላይ ሲገድሉ ሌሎችንም ማቁሰላቸው በዜና ማሰራጫዎች ተላልፏል። የሟቾቹን እሬሳና የቆሰሉትንም ሰዎች የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በአነዚሁ ድርጅቶች አማካይነት ተለቀዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ፤ የገዢው ክፍል ስለተፈጠረው ሁኔታ በራሱ የዜና ድርጅት በኩል መግለጫውን ሰጥቷል። እንደ ገዢዎቹ አገላለጽ፤ ጥቃቱ የተፈጸመው በተሳሳተ ማስረጃ ምክንያት ነው። ማለትም፤ በሦስት አቅጣጫዎች ወደሀገሪቱ ሊገባ የነበረውን የኦነግ ዘመቻ ለማክሸፍ ሲባል የተወሰደው እንቅስቃሴ የፈጠረው ስህተት ነው ባዮች ናቸው።

ይሁንና፤ የገዢዎቹን አገላለጽ ለማመን ያዳግታል። ምክንያቱም ጥቃቱ የተፈጸመው መሀል ከተማ ውስጥ ባልታጠቁ፤ ንጹሀን ሰዎች ላይ ነው። ድንበር ላይ አይደለም ጥቃቱ የተፈጸመው። ስለዚህ፤ ዛሬ በሞያሌ ከተማ የተፈጸመው የግፍ ግድያ ነገ ደግሞ በሌሎች ከተሞች ውስጥ፤ አዲስ አበባንም ጨምሮ፤ ሊከሰት የማይችልበት ምክንያት የለም።

በሞያሌ ለተፈጠረው ጥቃትና ላስከተለውም ስደት ዋነኛ ምክንያት በቅርቡ በሕወሀት ገዢዎች የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው። በአሁኑ ጊዜ በመላ ሀገሪቱ ውስጥ ለቀረበው የለውጥ ጥያቄ መፍትሄው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አይደለም። የሕወሀት ገዢዎች ይኽን መንገድ የመረጡበት ምክንያት እራሳቸውን በሥልጣን ላይ ለማቆየት እንደሆነ ግልጽ ነው።

እዚህ ላይ የሚያሳዝነው ነገር፤ የሕወሀት ገዢዎች ከነርሱ በፊት የነበሩት መሪዎች ካደረጉት ስህተት ሊማሩ አለመቻላቸው ነው። ለምሳሌ፤ እንደ አ. አ. አቆጣጠር በ1973/74 የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት በተናጋበት ወቅት፤ ህዝቡ ሰላማዊ ለውጥ በጉጉት ይጠበቅ ነበር።

የሹማምንቶቹ ዓላማ ግን በሥልጣን ላይ ለመቆየት የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ ሆነ። ይህም አሠራር ያስክተለው ውጤት ለነርሱም ሆነ ለህዝቡ የሚበጅ አልነበረም።

ከዚያም በኋላ የመጣው ወታደራዊ መንግሥት ከዚህ ዓይነቱ ስህተት ሊማር አልቻለም። የራሱን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም ሲል በወሰደው እርምጃ ምክንያት፤ ሀገሪቱ በማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቃ በመጨረሻ ከሁለት ልትከፈል በቃች። ዛሬ ኢትዮጵያን የሚገዛው ሕወሀት የዚያ ጦርነት ውጤት ነው።

የሕወሀት መሪዎች ለሀያ ሰባት ዓመታት ያህል በወታደራዊ ኃይል ሀገሪቱን ሲገዙ ከቆዩ በኋላ፤ በመጨረሻ ህዝቡ “አልገዛም በቃኝ” በማለት ዲሞክራሲያዊ ለውጥ በሰላማዊ መንገድ ከጠየቀ ሰንብቷል። ነገር ግን፤ ከዚህ በፊት እንደተለመደው ሁሉ፤ የሕወሀት ገዢዎች ወታደራዊ ኃይላቸውን እየተጠቀሙ ህዝቡን ለዘለዓለም ለመግዛት ይፈልጋሉ።

ይሁንና፤ ህዝቡ በህብረት ተነስቶ፤ “እምቢ፤ አልገዛም” ባለበት ሰዓት፤ የወታደር ኃይል መጠቀም ፋይዳ አይኖረውም። በመጀመሪያ ሊታወቅ የሚገባው ነገር፤ ሕወሀትንና ወታደሮቹን ህዝቡ የራሱ አድርጎ አያያቸውም። እንደወራሪ ኃይል ነው የሚቆጥራቸው።

ስለዚህ፤ የሕወሀት ወታደሮች ያለቦታቸው ነው የሚንቀሳቀሱት ማለት ነው። ስለሆነም፤ ኮሽ ባለ ቁጥር ጠመንጃቸውን እየተኮሱ ህዝቡን መፍጅት ይሆናል ሥራቸው።

ይህ ዓይነቱ መንገድ የሕወሀት ገዢዎችን በሥልጣን ላይ ሊያቆያቸው አይችልም። ህዝባዊ እምቢተኝነቱንም አያቆመውም፤ ይበልጥ ያጠናክረዋል እንጂ።

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ሰላማዊ ህዝባዊ እምቢተኝነት፤ ቁጥራቸው ትንሽ ነው የማይባል ወጣት ሰማእታትን ማስከፈሉ ቢያሳዝንም፤ ከዚህ በፊት ያልታዩ  ጠቃሚ ውጤቶች ሊያመጣ ችሏል።

አንደኛ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ህዝቡ በአንድ ዓላማ ላይ እንዲተባበር በማድረግ፤ ሰላማዊ የለውጥ ኃይል እንዲመሠረት አስችሏል። ሁለተኛ፤ አዲስ አስተሳሰብ ያላቸው መሪዎች እንዲፈጠሩ አድርጓል።

ሦስተኛ፤ የተባበረ ሰላማዊ የህዝብ ትግል ከትጥቅ ትግል የላቀ መሆኑን ህዝቡ፤ በተለይ ወጣቱ፤ እንዲገነዘብ አስችሏል። አራተኛ፤ የሕወሀት የውጪ ደጋፊዎች፤ እንደ አሜሪካን ያሉት ሀገሮች፤ በህዝቡ ጉደይ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ትኩረት እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል።

ለምሳሌ፤ ህዝቡ በነፃና ሰላማዊ መንገድ ሀሳቡን ለመግለጽ እንዲችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፍጥነት እንዲነሳ እነዚህ የውጪ ኃይሎች መጠየቃቸው ለዚህ በማስረጃነት ሊጠቀስ ይችላል።

በመጨረሻም፤ የሕወሀት ገዢዎች፤ በዘርና በልዩ ልዩ መንገዶች  የከፋፈሏትን ሀገር፤ የተጀመረው ህዝባዊ ትግል ህዝቡን እንደገና እንዲቀራረብ በማድረግ አብሮ የመኖርና የአንድነት ተስፋ እንዲኖረው አድርጎታል።

ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ስኬቶች ለኢትዮጵያ ህዝብ አበረታችና ትምህርታዊ ናቸው። ይህም ማለት፤ ህዝቡ እጅ ለእጅ ተያይዞ ከተነሳ፤ ለመሥራት የሚያቅተው ነገር አይኖርም። የተባበረን ህዝብ ወታደራዊ ኃይል በምንም ዓይነት ሊያሸንፈው አይችልም።

የሕወሀት ገዢዎች ይህን እውነት ተገንዝበው፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጃቸውን በፍጥነት በማንሳት፤ ለዲሞክራሲያዊ ሽግግር ከህዝቡ ጋር በእኩልነት ተሳታፊ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ፤ በሰላማዊ ህዝብ ላይ የሚፈጽሙት የግፍ ወታደራዊ ጥቃት ወደፊት ተጠያቂ  ሊያደርጋቸው ይችላል።