ትምህርታዊ ቪድዮ ኮንፈራንስ፤ ኦክቶበር 13 2017

ዶ/ር አሰፋ ምህረቱ

የጂኦግራፊ ሙሉ ፕሮፌሰር፤ ኤመረተስ

ሚሺጋን ስቴት ዪኒቨርስቲ

ኢትዮጵያ በሰላምና በዴሞክራሲ ለዘሌቄታ ህዝቦችዋን ለማስተዳደር ከፈለገች ከአማራጭ ፍቾች ውስጥ አንጋፋዎቹ ወደቀድሞው የአስተዳደር ከፍለ ሃገራት መመለስና እነሱን በፌደራላዊ ስርአት አዋቅሮ ህዝቡን በአንድ በማያወላውል የኢትዮጵያዊ ዜግነት ማዋሃድ ይሆናል።

ይህንንም የምለው፤ በሚከተሉት የማያከራክሩ ተጨባጭ ነጥቦች ላይ በመመርኮዝ ነው።  አነዚህ ነጥቦች ባለፉት ጥቂት አመታት ካሳተምኳቸው ሶስት ጥናቶች ውስጥ የተውጣጡ ናቸው።

የቀድሞ ከፍለሃገራት አብዛኛውን በተፈጥሮ ገጽታዎች (ማለትም፤ በወንዞች፡በተራራዎች፡ በሸሎቆዎች፡ ወዘተ…) (ካርታ Aን ይመልከቱ) የተከለሉ ሲሆኑ፤ እነዚህም የቀድሞው ድንበሮች (የኤርትራ ነጻ አውጪ ቡድኖች ከመፈጠራቸው በፊት) ለብዙ አመታት አለምንም ችግር ለማእከላዊና የውስጥ አስተዳደር ሲሰራባቸው የቆዩ ናቸው። አብዛኛዎቹ ድንበሮች የወንዝ ሸለቆዎች ስለነበሩ፣ እንደ አሁኑ ሰው-ፈጠር፤ ህዝቡን በጎሳ የሚለያዩ እጥሮች አልነበሩም (ካርታ Bን ይመልከቱ)።

የቀድሞ ከፍለሃገራት፤ ባጠቃላይ የኢትዮጵያን መሬቶችና የተፈጥሮ ሃብቶች (ዝናብ፣ወንዝ፣ ጫካ፣ የዱር ሃብቶች)፤ አንዲሁም በሃገሪቱ ዋና ዋና የአየርና የመልክአ-ምድር ጠባዮች፤ (ቆላ፣ ወይና-ደጋ፣ ደጋ)፡ ተካትተው ለሁሉም ህዝብ ኢንዲዳረሱ ያደረጉ ከመሆናቸውም በላይ፤ ከአስራ ሶስቱ ክፍለ ሃገሮች ውስጥ አስራ አንዱ የኢትዮጵያን የኢንተርናሽናል ድንበሮች ጥበቃ ድርሻቸውን እንድያበረክቱ የተዋቀሩ ነበሩ።

የቀድሞ ከፍለሃገራት፤ የህዝብ መቀላቀልን ሳይገድቡና ሳያዳክሙ፣ እያንዳንዳቸው በቁጥር ብዛት ይዘውት የነበረው ከኣንዳንድ ጎሳ የወጣ ብሄረሰብ ነበር። ለምሳሌ፣ ጎጃም (አማራ)፤ ትግራይ (ትግረ)፤ ወለጋ (ኦሮሞ)፡ ሐረር (ሶማሌ)፡ ወዘተ፣ ነበር። ይህም ማለት፤ የቀድሞዎቹ  የክፍለሀገር ድንበሮች የኢትዮጵያን ዋና ዋና ብሄረሰቦች (ጎሳዋች) ለመበረዝና ለማዳከም የተደረጉ የሴራ ንድፎች ወይም ዘዴዎች አልነበሩም። በነዚህም ክፍለሃገሮች ውስጥ፡ በጎሳ ወይም በብሄረሰብ የተደራጀ ውስጣዊ ወይም ድንበራዊ የጥቃት ግጭት በኢትዮጵያ ታሪክ ኖሮ አያውቅም።

የክፍለሃገር አስተዳደር አጠራር ዘይቤዎች ቀደም ብሎ ከነበሩት “ጠቅላይ ግዛቶች” ወደ “ክፍለሀገራት” ቢለወጡም፣ የጊዜው አሳቢ ምሁራንና የአንዳንድ ብሩህ የፖሊቲካ መሪዎች ምኞት፣ የማእከላዊ አስተዳደር የበላያ ቁጥጥርን የሚቀንስና የራስ አስተዳደርን የሚፈቅድ የፌደሬሽን አወቃቀር ነበር።  ይህ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በአሁኑ ሰው-ፈጠርና አለያይ፤ ጎሳዊ ክልል (አፓርታይድ) ስር ባልወደቀም ነበር።

የቀድሞ ከፍለሃገራት፤ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ዜግነት በላይነት በማያወላውል ሁናቴ አያስከበሩ፤ የሃገሪቱንም ህዝባዊ ስብስብ፤ እንዲሁም ዋና ዋና ታሪካዊ መታወቂያዎችን በአድነትና በኩራት አንዲከበሩ ያደረጉ ነበሩ፡፡

በተቃራኒው፣ የአሁኑ የጎሳ ክልላዊ ስርአት፣ የኢትዮጵያን ህዝብ በሁለት ዜግነት ውዥንብር ውስጥ አንዲገባና፣ የህዝቡ ማንነት እንዲሁም ታሪካዊ መታወቂያዎችና ቅርሶች ኢንዲሰባበሩና ኢንዲዋረዱ አድርጓል። “የመጀመሪያው የዜግነት ማንነቴ ኦሮሞ/አማራ/ሶማሌ ወዘተ … ነው ወይስ ኢትዮጵያ?” በሚል ቀውሳዊና አወላዋይ ችግር ውስጥ ሕዝቡ እንዲገባ አድርጓል።

የቀድሞው የክፍለሀገራት ስርአት፣ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የመታወቂያና የኩራት መድረክ ነበር። ለምሳሌ፤ የሲዳሞ ልጅ፣ የወለጋ ልጅ፣ የጎጃም ልጅ፣ የወሎ ልጅ፣ የትግሬ ልጅ፣ የሐረር ልጅ፣ የባሌ ልጅ፣. እየተባለ ማንነት በገሀድ ሲገለጽ ቆይቷል። ሕዝቡ በኢትዮጵያዊ ዜግነቱ ኮርቶ፤ ያለምንም እንቅፋት እንደልቡ በመላው አገሪቱ ውስጥ እየተዘዋወረ በፈለገበት ቦታ ይኖር፤ ይማርና ይሠራ ነበር።

የቀድሞ ከፍለሃገራት በአሁኑ የጎሳ ክልሎች መተካት፤ በጎሳ መለያየት ለሚያምኑና የኢትዮጵያን አንድነት ለሚጻረሩ ቡድኖች ትልቅ የመድረከ ሃይል አበርክቷል። ይህንንም መድረክ በመጠቀም፡ የጎሳ አቀንቃኞች በተለያዩ ታሪክ-ነጠቅ በሆኑ ተንኮል-አዘል የፈጠራ ትረካዎች የኢትዮጵያን ህዝብ ለመለያየት እየጣሩ ይገኛሉ።  ከነዚህም ተንኮል-አዘል የፈጠራ ትረካዎች በተለይ አደጎኞቹ የሚከተሉት ናቸው:

  1. ኢትዮጵያ ከመቶ አመት በፊት ያልነበረች “የፈጠራ” አገር ናት፤
  2. ኢትዮጵያ ከ 1974 መንግስተ-መፈንቅል በፊት ለተለያዩ ጎሳዎች “እስር ቤት” ነበረች፤
  3. ኢትዮጵያ ከ 1974 መንግስተ-መፈንቅል በፊት “በቅኝ አገዛዝ” ስርአት የምትመራ አገር ነበረች፤
  4. አማራና ትግረ “የገዢ መደብ” ሁነው የቀረውን የኢትዮጵያ ህዝብ በጭቆናና በመበዝበዝ ገዝተውታል።

እንዚህ ተንኮል-አዘል የፈጠራ ትረካዎች፣ በአውሮፓ አቆጣጠር ከ1960 አካባቢ ጀምሮ ዘመኑ የፈጠራቸው “አብዮታዊ” በሚል አድማስ ስር የተሰለፉ በሁሉን-አውቅባይ ምሁራን የተጸነሱ ሆነው ሳለ፣ በተጨማሪ የ1974 መፈንቅለ መንግስት ያበረከታቸው የኮሚንስትና የጎሰኛ ፖለቲከ ሃይሎች፣ ለ“ለያይቶ ማጋጨት” የአገዛዝ ስልት እንዲያመቻቸው፣ እነዚህን ተንኮል-አዘል የፈጠራ ትረካዎች በማጋነን ሲያስፋፏቸው ቆይተዋል።  እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን የፈጠራ ትረካዎች ማብራራት በዚህ መድረክ ላይ ባይቻልም፣ ነገሩን በዝርዝር ለመከተል ለሚሹ ሁሉ፣ በጥናታዊ ጆርናል የታተሙትን ጽሁፎቼን ከዚህ አሰተያየት መጨረሻ በዝርዝር ጠቅሻለሁ።

ከ1974 ጀምሮ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የተዘረጉት አስተዳደሮች ሕዝቡን በመከፋፈል እንዲጋጭና እንዲጣላ ከማድረጋቸው በስተቀር የጠቀሙት ነገር የለም። ሕዝቡ ተባብሮ በመሥራት ኑሮውን እንዲያሻሻል ከተፈለገ፤ ኢትዩጵያ ወደታሪካዊ ክፍለሀገራት በመመለስ በፌደራላዊ ራስገዝ ስርአት ደንብ መደራጀት ይኖርባታል።

አመሰግናለሁ።  

የኢትዮጵያ ዋና የአስተዳደር ክፍፍል ካርታዎች።

  1. ከ 1974 በፊት የነበሩት አብዛኛውን በመልክአ-ምድራዊ መሰረት የተዋቀሩ ክፍለ ሃገራት።
  1. ከ 1991 በኋላ ለጎሳ ስብስብ መለያያ የተዋቀሩ ክልሎች።

  1. Mehretu, Assefa. “Delegitimizing Multicultural Collective Identity in Ethiopia: A Critical Reflection on Ethnic Federalism.” Horn of Africa, Volume XXIX, 2011, pp. 64-82.
  2. Mehretu, Assefa. “Ethnic Federalism and its Potential to Dismember the Ethiopian State.” Progress in Development Studies, Volume 12, Nos. 2&3 (2012), pp. 113-133.
  3. Mehretu, Assefa. “Delegitimization of the Collective Identity of Ethiopianism” International Journal of Ethiopian Studies, Volume XI, No. 1 (2017), pp. 45-70.