አስተያየት

ከዶ/ር ዳንኤል ተፈራ

የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር፤ ኤመረተሰ።

በአሜሪካን ድምፅ ሬድዮ ጋዜጠኛ፤ በአቶ ሰሎሞን አባተና በቀድሞው  አምባሳደር፤ ሚስተር ኽርማን ኮኽን መካከል ከዚህ በላይ በተጠቀሰው አርእስት ላይ፤ በታህሳስ 22/ 2017፤ የተካሄደውን ቃለመጠይቅ  በጥሞና አዳምጫለሁ። ሰለአምባሳደሩና ባነሷቸው ጉዳዮች ላያ አስተያዬትን ለመስጠት እሞክራለሁ።

የአማባሳደር ኽርማን ኮኽንን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት፤ የዛሬ ሀያስድስት ዓመት ነው።  የአሜሪካን፤ የጆርጅ ኤች ቡሽ አስተዳደርን በመወከል፤ የኢትዮጵያ መንግሥትንና የሰሜን አማጽያንን አስታርቃለሁ ብለው፤ የለንደኑን ስብሰባ ለመምራት በሊቀመንበርነት ተሰይመው ነበር።

አምባሳደር ኽርማን ኮኽን፤ ቃል በገቡበት መሠረት፤ ሁለቱን ክፍሎች ሳያደራድሩ፤ “አማጽያኑ አዲስ አበባ ገብተው ያስተዳድሩን ኃላፊነት እንዲረከቡ ተደርጓል” ብለው፤ ለዓለም ጋዜጠኞች መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።

በስፍራው የነበረ አንድ ጋዜጠኛም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው። “የኢትዮጵያ መንግሥት ዋና ተወካይ (ጠ/ም ተስፋዬ ዲንቃ፤ አሁን በሕይወት የሉም) ውሳኔውን በመቃወም፤ ስብሰባውን ለመካፈል ፈቃደኛ አይደለሁም ማለታችውን ያውቃሉን” ብሎ ቢጠይቃቸው፤ “እርሳቸው አሁን አያስፈልጉም” ብለው መልስ ሰጡ።

ዋሽንግተን ከተመለሱ በኋላም፤ የተልኮአቸውን መሳካት ለአሜሪካን ኮንግረስ አስረዱ። “አንደኛው ክፍል ሌላውን በደንብ አድርጎ ስላሸነፈው፤ በአፍሪካ ቀንድ ከብዙ ጊዜ በኋላ ሠላም ለመጀመሪያ ጊዜ ሊሰፍን ችሏል፤ አሁን በረሀብ ለተጎዳው ህዝብ ምግብ ያለችግር ማከፋፈል ይቻላል” ሲሉ ተናገሩ።

የአምባሰደሩ ዋና ዓላማ ግን ይህ አልነበረም። የኢትዮጵያጵያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ወደዝምባብዌ እንዲሸኙና ሕወሀት ያልምንም ችግር አዲስ አበባ እንዲገባ፤ ከዚያ በኋላ፤ ወደአስራሦስት ሺህ የሚሆኑ ቤተእስራኤላዊያን በአስስቸኳይ ወደእስራኤል እንዲሄዱ ለማድረግ ነበር። ስለዚህ የለንደኑ ሰብሰባ፤ ይህን ዓላማ ለመሸፈን የተደረገ የዲፕሎማሲያዊ ሥራ ይመስላል።

ነገር ግን፤ የአምባሳደሩ ውሳኔ፤ ፍትህ የጎደለውና የኢትዮጵያን ህዝብ ከፋፍሎ የሚያጋጭ መሆኑን  በመፍራት፤ በወቅቱ የጻፍኩት የተቃውሞ ደብዳቤ፤ በኒውዮርክ ታይምስና በዋሽንግተን ፖስት ጋዜጦች መታተሙን ዛሬ ላስታውስ እወዳለሁ። በደብዳቤዬ እንድገለጽኩት ሁሉ፤ ቅሬታዬ፤ አምባሳደር ኮኽን ያስታራቂነት ቃላቸውን አለመጠበቃቸውና ከአሸናፊዎች ነን ባዮች፤ አማጽያን ጋር መወገናቸውን ነበር።

የአምባሳደር ኮኽን ስልት፤ በዲፕሎማሲው ዓለም የተለመደ የሥራ አፈጻጸም ሊህን ይችል ይሆናል። አስመስጋኝ ሥራም ሊሆን ይችል ይሆናል። አምባሳደር ኮኽንም ጎበዝ ዲፕሎማት ናቸው እየተባሉ በዋሽንግተን ይመስገናሉ። ይሁንና፤ ለዓለም የገቡትን ቃል አለማክበራቸው ግን ሊዘነጋ አይችልም።

አንድ ጊዜ፤  ቶማስ ጀፈርሰን፤ “ዲፕሎማት ማለት ምን ማለት ነው?” ተብለው ተጠይቁ ይባላል። እርሳቸውም ሲመልሱ፤ “ዲፕሎማት ማለት፤ ጨዋ ሰው ለሀገሩ ጥቅም የሚዋሽ” ብለው መለሱ ይባላል።

አስታሪቂነት የእውሸት ሥራ አይደለም። በኢትዮጵያ ታሪክ፤ የአስታራቂነት ሥራ፤ በማንኛውም ባህል ውስጥ ያለና የተከበረ ሥራ ነው። ያስታራቂነት ሥራ በቀላሉ ለማንም የማይስጥ፤ ለተወደዱና ለተከበሩ፤ ጨዋ ያገር ሽማግሌዎች ብቻ የሚሰጥ ኃላፊነት ነው።

አስታራቂነት “የአንተም ተው፤ የአንተም ተው” ሥራ ሳይሆን፤ አድሎ የሌለበት፤ የፍትህ ሥራ ነው፤ በኢትዮጵያ ደንብና ባህል። ስለዚህ፤ ለማንም ሳያዳሉ፤ ለፍትህ ብቻ የሚቆሙ ያገር ሽማግሌዎች በሕዝብ ዘንድ ሁልጊዜ የተከበሩ ናቸው።

ለምሳሌ የጉራጌ ሕዝብ፤ ያገር ሽማጌሌዎቹን፤ በፍጹም ፍህታዊነታቸው በጣም አድርጎ ያከብራል። “ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ያገር ሽማግሌ” እያለም ያደንቃቸዋል፤ ይወዳቸዋል።

አምባሳደሩ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ እርቅ መኖር አለበት ሲሉ ተደምጠዋል። ይህ መልካም አባባል ሆኖ ሳለ፤ በዳዩን ከተበዳዩ ለይተው ያወቁ አይመስሉም። ሕወሀትንና  ተቀናቃኞቹን እንደበዳይና ተበዳይ አድርገው ለማስታረቅ፤ “የሕወሀት መንግሥት ለአሜሪካን መንግሥት ያስታራቂ ያለህ ብሎ ደብዳቤ ይጻፍ” ባይ ናቸው።

ከሕወሀትና ከተቀናቃኞቹ የግል ጥቅም በፊት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ሊቀድም ይገባል። ተበዳዩ የትውልድ አገሩን  የተነፈገው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ (ከትግሬ በስተቀር) ሲሆን፤ በዳዩ የሕወሀትና የአሜሪካን የጥቅም ትስስር ያመጣው የዘር ፖለቲካ ነው።

የሕወሀትንና ያሜሪካንን መንግሥታት በጥቅም መተሣሠር ከአምባሳደሩ በላይ ጠንቅቆ የሚያውቅ ሌላ ሰው ያለ አይመስለኝም። የዚህ ትስስር መሥራች አባል እንደመሆናቸው መጠን፤ የግንኝነቱ ጠንቅ የኢትዮጵያን ህዝብ በዘር በመከፋፈልና እርሱ በርሱ በማጋጨት ምን ያህል እንደበደለው መገንዘብ ይገባቸው ነበር።

ላለፉት ሀያስድስት ዓምታት፤ የሕወህት የዘር ፓለቲካ፤ ጥቂቱን ጠቅሞ ብዙውን ጎድቷል። ስለዚህ፤ በኢትዮጵያ ህዝብ  ላይ የሚደርስው በደል ሊወገድ የሚችለው፤ የአሜሪካንና የሕወሀት መንግሥታት ግንኙነት ያመጣው ጸያፍና የሰውን ልጅ አዋራጅ የሆነው የዘር መከፋፈል ፓለቲካ ተወግዶ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ወደየራሱ ታሪካዊ ክፍለሀገሮች በመመለስ፤ በዲሞክራሲና በነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ተሳስሮ አብሮ ለመኖር እንዲችል ሲደረግ ብቻ ነው።