ዶ/ር ዳንኤል ተፈራ
የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር፤ ኤመረተስ

የዚህ ጽሑፍ ጽንስህሳብ፤ የክልል ስርአት ለዲሞክራሲ ሽግግር እንቅፋት ከመሆኑም በላይ፤ ኢትዮጵያን ወደፊት ጨርሶ ሊያጠፋት ይችላል የሚል ነው። ስለዚህ፤ ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና በኢትዮጵያ ውስጥ ሊመጣ የሚችለው የክልል ስርአት ተወግዶ ሀገሪቱ ወደዲሞክራሲ ስትሸጋገር ብቻ ነው። ይህ ጽሑፍ፤ በመጀመሪያ የክልል ስርአት ያሰከተላቸውን የኢኮኖሚ ችግሮች ከዳሰሰ በኋለ፤ በቅርቡ የታየው የአንድነት ኃይል ማንሰራራት ለዲሞክራሲ ሸግግር ሊፈጥር የሚችለውን ዕድል ይመለከታል።

ለመግቢያ ያህል፤ ከኢጣሊያን አጭር የቅኝ አገዛዝ ዘመን በስተቀር፤ ዘርን ወይም ቋንቋን መሠረት ያደረገ የክልል ስርአት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ አዲስ ነገር ነው። ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዘር ወይም ብሔር በሚሉት ልትከፋፈል የቻለችው፤ የሰሜን አማጽያንና ግብረ አበሮቻቸው በጊዜው የነበረውን ወታደራዊ መንግሥት በጦር ኃይል በማሸነፍ በምቱኩ የብሔርተኛ መንግሥት ሊመሰርቱ በመቻላቸው ነው። ስለዚህ፤ የጦር አሸናፊዎቹ የኢትዮጵያን መሬት ለራሳቸው ለማከፋፈል ሲሉ ለረጅም ጊዜ ሀገሪቱን በሰላም ያገለገለውን የክፍለሀገር አስተዳደር አፈራርሰው በክልል ስርአት በመተካታቸው፤ ይኸው አሁን ኢትዮጵይን ለማያቋርጥ ትርምስና ፍጅት ዳርገዋታል።

ለምሳሌ፤ በክልሎች መካከል እንዲሁም በክልሎች ውስጥ በየጊዜው የሚነሱ መሬትን ሳቢያ ያደረጉ ግጭቶች፤ ለህዝብ መፈናቀል እንዲሁም ለነፍስና ለንብረት መጥፋት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው። በሀገሪቱ ደቡብ በኩል በሶማሌና በኦሮሞ፤ በሰሜን ደግሞ በትግሬና በጎንደር እንዲሁም በትግሬና በወሎ መካከል እስካሁን መፍትሔ ያላገኙት ግጭቶች የክልል ስርአት የወለዳቸው ናቸው። ዛሬ በሀገሪቱ ውስጥ ሰላምና የረባ ኢኮኖሚ አለመኖር እንዲሁም የሥራ ዕድል መጥፋት ከክልል ስርአት ጋር ይያያዛሉ። የክልል ስርአት የሀገሪቱን የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ሀብት አባክኗል። ገበያዎች እንዲከፋፈሉ በማድረግ ህዝቡን በታትኗል።

የክልል ስርአት ከመመስረቱ በፊት፤ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ጥቅም የተሳሰረች አንድ ሀገር፤ አንድ መንግሥት ነበረች። ለምሳሌ፤ ድሮ የወለጋ የኢኮኖሚ ትስስር ከጎጃም ጋር ነበር። ዛሬ ወለጋ፤ ኦሮሚያ በሚሉት ውስጥ ተካሏል። ጎጃም ደግሞ የአመራ ክልል ተደርጓል። ስለዚህ፤ በሁለቱ ክፍለሀገሮች መካከል ለዘመናት የነበረው የኢኮኖሚ ግንኙነትና ጥቅም እንዲቋረጥ ተደርጓል ማለት ነው። በዚሁ አንፃር፤ ዛሬ በኦሮሚያ ውስጥ የተካለለው ቦረና፤ ለብዙ ዘመናት በጥቅም ተሳሰሮ የኖረው ከአካባቢው ህብረተሰቦች ጋር እንጂ፤ በርቀት ካለው ከኢሉባቦር ወይም ከወለጋ ጋር አልነበረም።

ሌላው ክልል ያስከተለው ችግር፤ በክልሎቹ መከካል የተፈጠረው የስፋትና የተፈጥሮ ሀብት ልዩነት ነው። ለምሳሌ፤ ሀረሪ የሚባለው ክልል በጣም ከማነሱ የተነሳ፤ በመልክአ ምድር ሰሌዳ ላይ ሞኖሩን እንኳን ማወቅ ያዳግታል። ስለዚህ፤ የህዝቡ ቁጥርና ፍላጎት በጨመረ ቁጥር፤ የመፈናፈኛ ቦታና የሥራ እድል ስለማይኖር፤ ድህነት ይባባሳል ማለት ነው።

የስፋት ማነስ ብቻ ሳይሆን፤ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብትም የሚያስከትለው የኢኮኖሚ ችግር አለ። ምክንያቱም፤ የተፈጥሮ ተሰጦ ካልተሠራበት ሀብት አይሆንም። ለምሳሌ፤ የኢትዮጵያ ለም የተፈጥሮ ሀብት በብዛት ያለው ኦሮሚያና ደቡብ ብለው በሚጠሯቸው ክልሎች ውስጥ ነው። ነገር ግን፤ ይህ ጥሬ ሀብት አልተሠራበትም። እነዚህ ክልሎች እንደስፋታቸውና የተፈጥሮ ሀብት መጠናቸው፤ በቂ የሰው ኃይልና ካፒታል የላቸውም። ይህ ሆኖ ሳለ፤ እነዚህ ቦታዎች ለሌላው በመከልከላቸው፤ በክልሎቹ ውስጥ የተፈጠረው የሰው ኃይልና የካፒታል ክፍተት ሊሟላ አልቻለም። በተጨማሪ፤ መሬት በግል መልክ ባለመከፋፈሉ፤ የእህልና የከብት እርሻን አጣምሮ ማረስ አልተቻለም። ስለዚህ፤ ሰፋፊ ቦታዎች ለግጦሽ ብቻ በመዋል ይባክናሉ።

የክልል ስርአት፤ ካፒታል እንዳይስፋፋ ከማድረጉ ጋር ተያይዞ፤ የሰውን ልጅ እንደልብ በመዘዋወር ሠርቶ ለመኖር የሚያስችል የተፈጥሮ ነፃነት ይከለክላል። አንድ ግለሰብ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት ቢፈልግ፤ የሕይወትም ይሁን የንብረት ዋስትና የለውም። “ከክልሌ ውጣልኝና ወደራስህ ክልል ሂድ” ነው የሚባለው። ስለዚህ፤ እርስበርስ በመማር ሀብት ማዳበር አልተቻለም።

የክልል ስርአት ከመጣ በኋላ፤ የቀድሞ የገጠር ከተማዎች ዛሬ ቀዝቅዘዋል፤ አንዳንዶቹም ጨርሰው ጠፍተዋል። የእነዚህ ከተማዎች መዳከም፤ ከዚህ በፊት በከተማና በገጠር መካከል የነበረውን የኢኮኖሚ ግንኙነትና ጥቅም እንዲቋረጥ አድርጓል። ለምሳሌ፤ አንድ ነጋዴ ወይም ሌላ ታታሪ ግለሰብ ገጠር ውስጥ ገብቶ መሬት በመግዛትና የራሱን መዋለንዋ በማፍሰስ ዘመናዊ እርሻ አልምቶ እራሱንና ህብረተሰቡን ለመጥቀም አይችልም።

ለማስታወስ ያህል፤ ኢትዮጵያ፤ የምግብ ክፍተት ያላት ሀገር ናት። ይህም ማለት፤ በየዓመቱ ወደውጪ ከምትልከው ይልቅ ከውጪ የምታስገባው ምግብ ይበልጣል ማለት ነው። ይህ ዓመታዊ ክፍተት ከአንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ይሆናል። ስለዚህ፤ በሀገሪቱ ላይ የሚያንጃብበው የረሀብ ወረረሽኝና የህዝብ እልቂት አሁን በሚገኘው የአሜሪካን የእህል እርዳታ ለዘላለም መሸሸግ አይቻልም።

ወደ ክልል ስርአት እንመለስና፤ ቀድሞ በተለያዩ ከተማዎች ይገኝ የነበረው የምርትና የሥራ እድል፤ ዛሬ ከአንድ የክልል ከተማ አያልፍም። በሰሜን ኢትዮጵያ፤ ባህር ዳር ውስጥ ያለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፤ በደብረ ማርቆስ፤ ጎንደርና ደሴ ላይ አይታይም። በደቡብ ኢትዮጵያ፤ ሀዋሳ ላይ ብቻ ነው ትኩረቱ ያለው። ያም ቢሆን፤ የመዝናኛ እንዱስትሪን እንጂ የአካባቢውን ሰፊ የእርሻ ተሰጦ ያማከለ አይደለም።

የበፊት ክፍለሀገሮች ዋና ከተማዎች በመታጠፋቸውና ሥልጣን በጥቂት ቦታዎች ታፍኖ በመያዙ፤ አስተዳደሩ ከህዝቡ ርቋል። ይህም ህዝቡ በራሱ ኢኮኖሚና ጉዳይ እንዳይሳተፍ ከማድረጉም በላይ የማያስፈልግ የገንዘብ ወጪና የሥራ ጊዜ መባከንን አስከትሏል። ለምሳሌ፤ የወለጋ ገበሬ ወይም ነጋዴ ጉዳይ ካለበት፤ አጠገቡ ያለውን ነቀምቴን ትቶ አዳማ ድረስ ለመሄድ ይገደዳል ማለት ነው። እንደዚሁም፤ የጎጃም ባለጉዳይ ደበረ ማርቆስን ትቶ ባህር ዳር ይሄዳል። የገሙ ጎፋውም፤ አርባ ምንጭ በመሄድ ፈንታ ሀዋሳ መሄድ ይኖርበታል።

የንግድ እንቅስቃሴና የመንግሥት ፕሮግራሞች በጥቂት የክልል ከተማዎች መወሰናቸው ሌሎች ችግሮችን አስከትሏል። የህዝቡ ቁጥር ከልክ በላይ እያደገ በመሄዱ፤ የሥራ እድል ፍለጋ እነዚህን ከተሞች አጨናንቋቸዋል። በዚህም ሳቢያ፤ የምግብና የቤት ኪራይ ዋጋ ከመናሩ የተነሳ፤ ብዙው ህዝብ በችግር ነው የሚኖረው።

የህዝብ ቁጥር ፍንዳታ ከተነሳ ዘንድ፤ የችግሩ አንደኛው ምክንያት ሀገሪቱ ለረጅም ጊዜ የተጠመደችበት ከእጅ ወደአፍ ኢኮኖሚ ወደ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ እስከአሁን አለመሸጋገሩ ነው። በመሆኑም፤ የህዝብ ቁጥር መጨመር ድህነትን ከማስፋፋት በቀር ገበያ ሊፈጥር አልቻለም። በአሳሳቢ ሁኔታ በማደግ ላይ ያለው የጫት ሱስ የፈጠረው የጫት ገበያ ብቻ ነው። ከዚህ የሚገኘውም ከፍተኛ ያገርና የውጪ ንግድ ትርፍ፤ ገበሬውን ከእህል ይልቅ ጫት አብቃይ እያደረገው በመሄድ ላይ ይገኛል።

ክልል፤ ብሔርተኞች የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚያስከብሩበት ስርአት ነው። ይህ ዓይነቱ ስርአት ለሀገሪቱ የተሻለ ውጤት አላመጣም። ዛሬ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚና ቀጣይነት አደጋ ላይ የጣለው፤ ብሔርተኞች የፈጠሩት የክልል ስርአት ነው። የሁሉንም ህብረተሰብ ጥቅም በእኩልነት ለማስከበር የሚቻለው፤ ዲሞክራሲያዊ ሸግግር ሲኖር ነው። ያ ደግሞ በብሔርተኞች ፈቃደኛነት አይመጣም። ምክንያቱም በሞኖፖሊ የያዙትን የግል ጥቅም ይነካባቸዋል።

ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ሊመጣ የሚችለው በህብረተሰቡ ውስጥ የብሔርተኞችን ኃይል ለመገደብ የሚያስችል ሌላ ኃይል ሲኖሩ ብቻ ነው። ስለዚህ፤ ለብዙ ዓመታት በገዢው መንግሥት ተጨቁኖና ተገፍቶ የቆየው የአንድነት (አንድ ህዝብ፤ አንድ ኢትዮጵያ) ኃይል በአሁኑ ሰዓት መጠናከር መጀመሩ ለዲሞክራሲያዊ ሽግግር በጣም አስፈላጊ ነው።። የአንድነቶች መጠናከር በብሔርተኞች ላይ ግፊት በመፍጠር፤ ለዲሞክራሲያዊ ሽግግር ዕድል ሊከፍት ይችላል።

የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሸግግር ሦስት መሰረታዊ ጥያቄዎችን ከግንዛቢ ማስገባት ይኖርበታል። አንደኛው ጥያቄ፤ ህብረተሰቡ በዘር ወይም በቋንቋ ሳይከፋፈል እንደገና እንዲደራጅ ማድረግን ይጠይቃል። የኢትዮጵያ ህዝብ በዘር ክልሎች በመታጠሩ፤ በሀገሪቱ ውስጥ በነፃ ተዘዋውሮ በእኩል ዜግነት ሠርቶ ለመጠቀም አልቻለም። በተጨማሪ፤ የክልል ወሰኖች በአብዛኛው ህዝብ ተቀባይነት ስለሌላቸው፤ በተለያዩ ቦታዎች የግጭትና የጥፋት መንስኤዎች ሆነዋል። የክልል ስርአት፤ ህዝቡን ከመብት ይልቅ ለመሬት ነጠቃና ለግዛት መስፋፋት እንዲታገል አድርጎታል።

ሁለተኛው ጥያቄ፤ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ቋንቋና ባህል ባከበረ መልኩ፤ ብሔራዊ አንድነትን ስለማጠናከር ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ የብዙ ባህሎችና ቋንቋዎች ሀገር እንደመሆንዋ መጠን፤ ብሔራዊ አንድነትዋ ሁሉን አቀፍና የጠነከረ ሊሆን የሚችልበት መንገድ ሊፈለግ ይገባል።

ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካና የደቡብ እሲያ ሀገሮች የታደለች ሀገር ናት። ማለትም፤ በመላው ሀገሪቱ ውስጥ ለብዙ ዘመናት ህዝቡን ያገናኘና ያስተሳሰረ የራስዋ የሆነ የአማርኛ ቋንቋ አላት። በተጨማሪም በአንዳንድ ቦታዎች በስፋት የሚነገሩ ቋንቋዎቸ አሏት። እነዚህ ቋንቋዎች እንዲዳብሩና እንዲታቀፉ ቢደረጉ የሀገሪቱን አንድነት በይበልጥ ሊያጠነክሩ ይችላሉ።

ሦስተኛው ጥያቄ የመሬት ባለቤትነትንና የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን ይመለከታል። በህብረተሰቡ ውስጥ ድህነትን ለማጥፋት የሚቻለው ፍትሀዊ የሆነ የመሬት ማከፋፈል ፕሮግራም በሥራ ላይ በማዋል በድህነት የሚማቅቀውን ህዝብ የንብረት ባለቤት በማድረግ ነው። መሬት እስከዛሬ የመንግሥት ሞኖፖሊ ሆኖ ቆይቷል። ማንኛውም ግለሰብ በነፃ ገበያ ሠርቶ የኑሮ ደረጃውን ሊያሻሽል የሚችለው የመሬትና የንብረት ባለቤትነት በህግ ተደንግጎ በሥራ ላይ ሲውል ብቻ ነው።

በመጨረሻም መጠቀስ ያለበት ጉዳይ አለ። ይኸውም፤ አሁን ህዝቡ እንዲህ ሆኖ በተከፋፈለበት ሰዓት፤ ምርጫ ማካሄድ የዲሞክራሲ ሽግግር አያመጣም። ከሆነም፤ የምርጫውን ውጤት አስቀድሞ መገመት አያዳግትም። የብሔርተኞችን እጅ ይበልጥ በማጠናከርና የርስበርስ እልቂትን በማባባስ፤ የሀገሪቱን መፈራረስ ሊያፋጥን ይችላል። በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ሊኖር የሚችለው፤ በመጀመሪያ በብሔርተኞችና በአንድነቶች መካከል ከዚህ በላይ ለተነሱት ጥያቄዎች ቋሚ ስምምነት ላይ ለመድረስ ከተቻለ ብቻ ነው።