ዶ/ር ዳንኤል ተፈራ
የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር፤ ኤመረተስ

የዚህ ጽሑፍ አርእስት የአሁኑ ጠቅላይ ምኒስትር እንደ አዲስ አስተሳሰብ አድርገው ለህዝብ ያቀረቡት ነው። አባባሉ፤ ከወትሮው ጸረኢትዮጵያ፤ ጸረአማራ ፕሮፓጋንዳ ጋር ሲነጻጸር፤ እርግጥም አዲስ አስተሳሰብ ሊያሰኝ ይችላል።

የጸረኢትዮጵያ፤ የጸረአማራ ፕሮፓጋንዳ የተቀየሰው በአንዳንድ የ1960ዎቹ መጀመሪያ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ነው። ዓላማውም የኢትዮጵያን ህዝብ በዘር ከፋፍሎ፤ በተለይ በሽዋ አማራ ላይ በማስነሳት፤ ሥልጣን ከመጨበጥ ያለፈ አልነበረም።

የኤርትራ ከኢትዮጵያ መለየትና የኢትዮጵያ ህዝብ በዘር መከፋፈል፤ የዚህ ፕሮፓጋንዳ ውጤቶች ናቸው። ከ1960ዎቹ ጀምሮ የመጣው ትውልድ፤ ይህን ፕሮፓጋንዳ እየተመገበ ነው ያደገው።

ከ1983 ዓ. ም. በኋላ፤ ኢትዮጵያ፤ የአንድ ሀገር፤ የአንድ ህዝብና የአንድ ዜግነት ታሪክ እንዳይኖራት ተደርጓል። መሬቷ ዘጠኝ ቦታ ተከፋፍሎ በዘር አጥር ተከልሏል። ይህን ስርአት በዋናነት በሀገሪቷ ላይ በጉልበት የጫኑት፤ የትገሬና የኦሮሞ ብሔርተኞች ናቸው።

ስለዚህ፤ ያሻቸውን ሰፋፊ መሬት ለራሳቸው ጥቅም ብቻ ለማድረግ ከልለው የያዙት ሁለቱ ብሔርተኞች ናችው። ለምሳሌ፤ የቀድሞው ትግሬ በታላቅዋ ትግራይ ተተክቷል፤ የጎንደርንና የወሎን ክፍሎች አካቶ። እንደዚሁም አርሲን፤ ባሌን፤ ኢሉባቦርንና፤ ወለጋን ይዞ፤ የሐረርጌን፤ የሲዳሞንና የሸዋን ክፍሎች ጨምሮ ኦሮምያ ተብሏል።

በእነዚህ አካባቢዎች ኢትዮጵያን ጨርሰው ሊያጠፉ የሚችሉ የዘር ግጭቶች ከጀመሩ ሰንብተዋል። አንደኛው በሀገሪቷ ሰሜን በኩል በአማራና በትገሬ መካከል ያለው ግጭት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ በኦሮሞና በሶማሌ መካከል የተቀሰቀሰው ጠብ ነው።

እነዚህ አራት ክፍሎች፤ በህዝብ ቁጥር ሰፊ ከመሆናቸው በላይ (ከትግሬ በስተቀር)፤ በታሪካቸው ኃይለኛ የሥልጣን ተፎካካሪዎች ናቸው (ትገሬና አማራ በተለይ)። ስለዚህ፤ በዘር መከፋፈላቸው፤ በመካከላቸው ከመቀራረብ ይልቅ መራራቅ እንዲካረር አድርጓል።

በአፍሪካ ውስጥ፤ የረጅም ጊዜ ታሪክ ካላቸው ሀገሮች መካከል የተረፈችው ኢትዮጵያ ብቻ ናት። የተቀሩት፤ በውስጥ የእርስበርስ ጦርነትና በውጪ የጠላት ወረራ ጠፍተዋል። ኢትዮጵያ ግን በህዝቧ ጥንታዊ ትስስርና አንድነት እስከዛሬ ልትኖር ችላለች።

ይሁንና፤ በህገ መንግሥት የተደነገገው የዘር ክልል፤ ይህንን የረጅም ጊዜ ትስስር በማናጋት፤ የኢትዮጵያን ህልውና ከአደጋ ላይ ጥሎታል። የኢትዮጵያ ህዝብ በዘር ተካሎ በሰላም ሊኖር አይችልም። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ውስጥ ያልተቀላቀለ ዘር፤ ያልተደራረበ መሬት የለም።

የዘር ክልል የተደነገገው ለገዥዎቹና ለደጋፊዎቻቸው የግል ጥቅም እንጂ ለህዝቡ ታስቦ አይደለም። ህዝቡ “በዘር ከፋፍላችሁ አታጋድሉን” እያለ ሲጮህ፤ መሪዎቹ የህዝቡን ችግር አይተው እንዳላዩ፤ ሰምተው እንዳልሰሙ በመሆን፤ በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት ነውና፤ ስለህዝቡ መከራ እምብዛም አልተጨነቁም። ተቃዋሚዎቹም ቢሆኑ የገዥዎቹን ቦታና ጥቅም ብቻ ነው አጠንክረው የሚመኙት፤ ከህዝቡ ጎን እንደመቆም ይልቅ።

እንዲህ ዓይነቱ እራስ ወዳድነት፤ በተለይ በመከራ ሰዓት፤ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ለማስታወስ ያህል፤ የሕወሀት ገዢዎች፤ የኤርትራዎቹንም ጨምሮ፤ አርበኛው ትውልድ በታላቅ እንክብካቤ ካስተማራቸው ወጣቶች መካከል ነበሩ። አርበኛው ትውልድ፤ ተወዳዳሪ የሌለው ባለውለታ ትውልድ ነው።

ይህ ትውልድ፤ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መሪነት እራሱን ሰውቶ ኢትዮጵያን ከፋሽት የጭቆና ቀንበር ያላቀቀ ትውልድ ነው። ከዚያም በኋላ፤ ሀገሩን እንደገና አቋቁሞ፤ ለራሱ ሳይማር፤ ልጆቹ ከርሱ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ በማሰብ ዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ ያደረገ ሀገሩን ወዳድ፤ ህዝቡን ወዳድ ትውልድ ነበር።

“ትምህርት ቤት የሠራንላችሁ፤ አስተማሪ የቀጠርንላችሁ፤ በትምህርት ታንጻችሁ ሀገራችሁን እንድትረዱ ነው።” የሚለው የንጉሠ ነገሥቱ የአደራ ቃል ከብዞዎቻችን አዕምሮ ውስጥ ቢፈለግ አይጠፋም። በዚህን ጊዜ ተማሪ የነበረ ሁሉ፤ “ለምን ትማራለህ? ተብሎ ሲጠየቅ፤ “ሀገሬን ለመርዳት ነው” ነበር መልሱ።

ይህ ትውልድ (በግምቱ ከ1930 እስከ 1960 ባለው ጊዜ ውስጥ የተወለደው)፤ ከጀግናው ትውልድ የተሰጠው አደራ፤ ባገኘው ዘመናዊ ትምህርት ተጠቅሞ እራሱን ብቻ ሳይሆን አገሩንም እንዲረዳ ነበር። ይሁንና፤ በሳይንሳዊ ምርምር ለሀገሪቱ የሚጠቅም እውቀት ከማመንጨት ይልቅ፤ ህዝቡን አንዴ በመደብ፤ አንዴ በዘር አይዲዮሎጂ በመከፋፈል በራሱ ጥቅም ላይ ብቻ ሲያቶክር ቆይቷል።

ዛሬ ኢትዮጵያን በመምራት ላይ የሚገኘው ትውልድ የቀድሞውን ራስ-ወዳድ ትውልድ የመደብና የዘር አይዲዮሎጂ ተቀብሎ ነው ያደገው። “ኢትዮጵያ እኔ ነኝ፤ ኢትዮጵያ አንተነህ፤ ኢትዮጵያ አንቺ ነሽ” ማለት ለኢትዮጵያ ህዝብ አዲስ አይደለም። ህዝቡ በተደጋጋሚ ላነሳቸው የዘር ክልል፤ የመሬትና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች መልስ ሊሆን አይችልም። የዚህ ትውልድ ውጤት ሊለካ የሚችለው የኢትዮጵያ ህዝብ ያነሳቸውን ጥያቄዎች በቆራጥነት መመለስ ሲችል ብቻ ነው።