ዶ/ር ዳንኤል ተፈራ

የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር፤ ኤመረተስ

ኢትዮጵያን፤ ከውስጥም ይሁን ከውጭ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮች ሊያድን የሚችለው ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ብቻ ነው። ከውስጥ የሚታየው የእርስበርስ ብጥብጥና የኢኮኖሚ ድክመት የውጭ ኃይሎችን ይጋብዛል። ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ ታሪክ ተደጋግሞ ታይቷል። በቅርቡም ከግብፅ ጋር የተነሳውን ውዝግብ በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። ይሁንና የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግር ውስጣዊ ነው፤ የውጭ ኃይል አይደለም። ስለዚህ፤  በአሁኑ ሰዓት ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ከሁሉም ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ከዚህ ቀጥዬ ዲሞክራሲያዊ ሽግግርን በተመለከተ የኢትዮጵያን የወደፊት ዕድል ለማስረዳት እሞክራለሁ።

ኢትዮጵያ ለምን እስካሁን ወደዲሞክራሲ ለመሸጋገር እንዳልቻለች ለመረዳት ከፈለግን፤ ከ1983 ዓ. ም. መጀመር ይኖርብናል። በ1983 ዓ. ም. የዓለም ፖለቲካ ሲቀየር፤ ኢትዮጵያ ወደ ዲሞክራሲ የመሸጋገር እድል አላጋጠማትም። ምክንያቱም፤ የተደራጀ ዲሞክራሲያዊ ኃይል ስለአልነበራት የሰሜን አማጽያንን መግታት አልተቻለም። ስለዚህ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሀገሪቱን የሚመራው፤ በጦርነት ያሸነፈው የብሔርተኞች መንግሥት ነው።

ስለዚህ፤ “የዲሞክራሲያዊ ሽግግር አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ እንዴት ሊመጣ ይችላል?” ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ወደ መልሱ ከማምራቴ በፊት፤ በአንዳንድ ከሽግግር ጋር ተያይዘው በሚነሱ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ላይ አስተያየት እሰጣለሁ። በመጀመሪያ፤ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር በገዢው መንግሥት ፈቃድና አማክኝነት ይመጣል ብለው የሚያስቡ አሉ። ይህ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም፤ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር የራሱን የገዢውን መንግሥት ጥቅም ስለሚጎዳ ነው። ማንኛውም መንግሥት ቢሆን ሥልጣኑን ለሌላ አሳልፎ አይሰጥም። ዲሞክራሲያዊ ሽግግር በመንግሥት ፈቃድና ፍላጎት የሚመጣ ቢሆን ኖሮ፤ የቀድሞዎቹ መንግሥታት ያመጡት ነበር።

ሁለተኛ፤ የሽግግር መንግሥት ቢቋቋም ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ያመጣል የሚሉ አሉ። የሽግግር መንግሥት መቋቋም በራሱ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር አያመጣም። በባዶ ሜዳ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ማለት ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ሊሆን አይችልም። ገዢው መንግሥት እራሱን በፈቃዱ አፍርሶ የሽግግር መንግሥት አይመሠርትም። የፖለቲካ ፓርቲዎች ነን የሚሉትም ቢሆኑ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም የሚያስችል ኃይል የላቸውም። ለምሳሌ፤ ከአቅም ማነስ የተነሳ በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግሥት ጥገኛ በመሆን ነው የሚንቀሳቀሱት።

ከሽግግር ጋር በተያያዘ ሌላው የሚነሳው የተሳሳተ አስተሳሰብ፤ ምርጫ መካሄድ አለበት የሚለው ነው። በመጀመሪያ ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ የዜጎች እኩልነት የለም። የዜጎች እኩልነት ሳይኖር ምርጫ ማካሄድ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር አያመጣም። በቀዳዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ለህግ መምሪያ ምክር ቤት ተወካይነት ምርጫዎች ይካሄዱ እንደነበር አስታውሳለሁ። ይሁንና ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሀገር አልነበረችም። በመሬት ባለቤትነት ላይ የተመሠረተ የበላይነትና የበታችነት ደረጃ የነበረባት ህብረተሰብ ነበረች።

ከዚያም በኋላ የመጣው ወታደራዊው መንግሥት  መሬትን በእጅ በማድረግ፤ መንግሥትን የበላይ፤ ህዝቡን ደግሞ የበታች ነው ያደረገው። ምርጫዎችን ግን አካሂዷል። አሁን ያለው  መንግሥት ደግሞ መሬቱን በብሔር ከፋፍሎ ይዟል። ስለዚህ፤ ክልል ያለው ብሔርተኛ የመሬት ባለቤትና የበላይ፤ የተቀረው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠረው ክልልና መሬት የሌለው ኢትዮጵያዊ ድግሞ የበታች ሆኗል። እንዲህ ዓይነት ጉልህ መበላለጥ በሚታይበት ሕብረተሰብ ውስጥ ምርጫ እናካሄዳለን ማለት፤ ጋሪውን ከፈረሱ በፊት እንደማስቀደም ይቆጠራል።

ምርጫ በየትኛውም ሀገር ለተለያዩ ምክንያቶች ይደረጋል። ለምሳሌ፤ በሰለጠነውና እኩልነት ባለበት ዓለም፤ ህዝብ  ያለፍርሀትና ተጽእኖ  መሪዎቹን ይመርጥበታል። ባልሠለጠነውና እኩልነት በሌለበት ዓለም ደግሞ፤ ምርጫ ገዢውን መንግሥት በሥልጣን ላይ ማቆያ ሽፋን ሊሆን ይችላል። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ በበላይነት ሥልጣን የጨበጠው የብሄርተኞች ክፍል መሆኑ ግልጽ ነው። ስለዚህ፤ ምርጫ  ማካሄድ የብሔርተኞችን የበላይነት አይቀይረውም።

ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ሊመጣ የሚችለው ለጥቅማቸው ሲሉ በእኩልነት በሚደራደሩ ተመጣጣኝ ኃይሎች ነው። ስለዚህ፤ “እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ  ወይ?” ብለን እራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት የማይመጣጠኑ ክፍሎች ወይም ጎራዎች አሉ ማለት እንችላለን። አንደኛው የኢትዮጵያዊያን ጎራ (አንድ ሀገር፤ አንድ ህዝብ የሚለው) ሲሆን፤ ከተለያዩ ህብረተሰቦች የተውጣቱ ግለሰቦችን ይይዛል። ሁለተኛው ጎራ ደግሞ በጦር ኃይል አሸንፎ ሥልጣን የጨበጠው የብሔርተኞች (ክልሎችና ህዝቦች የሚለው) ጎራ ነው። ሁለቱም ጎራዎች በውስጣቸው አንድነት የላቸውም። የሚያስተባብራቸው ነገር ቢኖር፤ አንደኛው ጎራ ለሌላኛው ጎራ ያለው ጥላቻ ብቻ ነው።

የኢትዮጵያዊያንና የብሔርተኞች ልዩነት የሀገሪቱ የታሪክ ጉዞ ያመጣው ስለሆነ ፍቆ ማጥፋት አይቻልም። እንዲያውም ይህ ከታሪክ የመጣ ልዩነት፤ በጥንቃቄ ከተያዘ፤ ለዲሞክራሲያዊ ሽግግር አመቺ ዕድል ሊፈጥር ይችል ይሆናል። ይሁንና፤ ይህ ሊሆን የሚችለው በሀገሪቱ ውስጥ ሙሉ የፖለቲካ ነፃነት ሲኖር ነው። ለምሳሌ፤ ገዢውን መንግሥት ለሚቃወሙ ድርጅቶች፤ የፓለቲካ ነፃነት አልተፈቀደም። ባልደራስ ላይ የሚደረገውን ተጽእኖ መጥቀስ ይቻላል። ገዢው መንግሥት “ዲሞክራሲ” የሚለውን ቃል በመደጋገም ያነሳል። ይሁንና፤ ሁለት ዓይነት ዲሞክራሲ የለም። ዲሞክራሲ አለ የሚባለው በህግ የተጠበቀ፤ በነፃ የመቃወም መብት ሲኖር ብቻ ነው። ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ያለፍርሀት ማቋቋም ሲቻል ነው።

ብሔርተኞች ሥልጣን ከጨበጡበት ጊዜ አንስቶ፤ በኢትዮጵያዊያን ላይ አድሎና በደል መፈጸሙ ከማንም የተሰወረ አይደለም። ይህ ዓይነት የተዛነፈ ድርጊት ለሀገሪቱ ዲሞክራሲ አላስገኘም። ሊያስገኝም አይችልም። በሌላ በኩል፤ ይህ በደል የፈጠረው ብሶት የኢትዮጵያዊያን ጎራ እንዲነሳሳ በማድረግ ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያዊያን ጎራ መጠናከር ለሀገሪቱ ጠቃሚነት አለው። ይኸውም፤ የተጠናከረ የኢትዮጵያዊያን ጎራ የብሔርተኞችን ብቸኛ ኃይል በመግታት ለዲሞክራሲያዊ ሽግግር የድርድር ዕድል ሊከፍት ይችላል።

የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር በአንድ ጎራ የበላይነት ሊመጣ አይችልም፤ ምክንያቱም ማንኛውም ጎራ ቢሆን የሚያስቀድመው የራሱን ጥቅም ብቻ ስለሆነ ነው። ሁለቱም ጎራዎች በእኩልነት መደራደር ይኖርባቸዋል፤ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲመጣ ከተፈለገ። በሁለቱም ጎራዎች መካከል የኃይል መመጣጠን ካለ፤ ለጥቅማቸው ሲሉ እንዲደራደሩ ይገደዳሉ። ዲሞክራሲያዊ ሽግግር፤ ለራስ ጥቅም ሲሉ ከራስ ደበኛም ጋር ቢሆን አብሮ ለመኖር መገደድ ማለት ነው። ያለበለዝያ ሁለቱ ጎራዎች ለግል ጥቅማቸው ብቻ ሲፎካከሩ ሊጠፋፉ ይችላሉ። ኢትዮጵያም ልትፈራርስ ትችላለች። ይህ አደጋ ሊወገድ የሚችለው፤ የሀገሪቱ መሠረታዊ ጉዳዮች በሁለቱ ጎራዎች ሠላማዊ ድርድር ቋሚ ስምምነት ከተበጀላቸው ነው። እነዚህም ጉዳዮች፤ የመሬት ባለቤትነት፤ የእኩል ዜግነትና ራስገዝነትን ማእከል ያደረገ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ናቸው። ሁለቱም ጎራዎች የሚያገኙት ጥቅም መኖር አለበት። ነገር ግን፤ ማንኛውም ጎራ ቢሆን የጠየቀውን ሁሉ ማግኘት አይችልም።l