ዶ/ር ዳንኤል ተፈራ
የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር፤ ኤመረተስ

የዚህ ጽሑፍ አርእስት፤ ጠቅላይ ምኒስትር አብይና ባልደረቦቻቸው ሊያመልጡት የማይችሉት የጊዜው ዋነኛ ጥያቄ ነው። ለመግቢያ ይሆን ዘንድ፤ በመጀመሪያ ጠቅላይ ምኒስትሩ እስካሁን ያከናወኗቸውን መልካም ሥራዎች ላስታውስ እፈልጋለሁ።

አንደኛ፤ እስከ ዛሬ ድረስ፤ በህዝቡ ላይ ሲፈጸሙ ለቆዩት ግፎችና ዘረፋዎች ጠቅላይ ምኒስትሩ፤ እራሱኑ ገዢውን መንግሥት ኃላፊና ተጠያቂ አድርገዋል። ስለዚህ፤ ለሀያ ሰባት ዓመታት ህዝቡን አስጨንቆትና አሸማቆት የኖረው ያለአግባብ የመታሰርና የመገደል ፍርሀት ተወግዶ የነፃነት አየር ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገሪቱ ውስጥ ሊነፍስ ችሏል።

ሁለተኛ፤ የፖለቲካ ልዩነቶቾ በግልጽ ውይይት እንጂ በሰው መግደል ሙያ እንደማይፈቱ በምሳሌዎች በማስረዳት፤ አዲስና የሠለጠነ የፖለቲካ ባህል እዲጀመር በሩን ከፍተዋል። ለማስረጃነት፤ የታሰሩት ፖለቲከኞች እንዲፈቱ አድርገዋል። ከሀገር ውጪም የነበሩ ፖለቲከኞች ወደሀገራቸው እንዲመጡና በነፃ እንዲንቀሳቀሱ ፈቅደዋል።

ሦስተኛው፤ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለሀያ ዓመታት ተቋርጦ የነበረው ግንኙነት እንደገና እንዲቀጥል ማድረጋቸው ነው። ይህ ግንኙነት ለሁለቱም ሀገሮች ሰፊ የኢኮኖሚ ጥቅም ሊያስገኝ ከመቻሉም በላይ፤ ለኢትዮጵያ ደህንነትና ሰላም እጅግ አስፈላጊ ነው። በተለያዩ ጊዜያት፤ የኢትዮጵያ ጠላቶች ኤርትራን መግቢያና መነሻ ማድረጋቸው አይዘነጋም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ጠቅላይ ምኒስትሩና ባልደረቦቻቸው ሊዘነጉት የማይችሉት፤ በየእለቱ በኢትዮጵያ ላይ የሚያንጃብበውን የመበታተን አደጋ ነው። ኢትዮጵያ በዘጠኝ የብሔር መንግሥታት ተከፋፍላለች። እነኝህ መንግሥታት ታማኝነታቸው ለራሳቸው ብሔር እንጂ ለኢትዮጵያ አይደለም። በፈለጉ ጊዜም ነፃነታቸውን እንዲያውጁ ተደርገው የተዋቀሩ ናቸው።

ለማስታወስ ያህል፤ ከኢጣሊያን አጭር የአገዛዝ ዘመን በስተቀር፤ የብሔር መንግሥት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ አዲስ ነገር ነው። ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በብሔር ልትከፋፈል የቻለችው፤ የሰሜን አማፅያንና ግብረአበሮቻቸው በጊዜው የነበረውን ወታደራዊ መንግሥት በጦር ኃይል በማሸነፍ፤ በምትኩ የብሔርተኞች መንግሥት ሊመሰርቱ በመቻላቸው ነው።

እነዚህ ብሔርተኞች የተባበሩበት አንድ ነገር ቢኖር፤ በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው የጋራ ጥላቻ ነው። ስለዚህ፤ ለረጅም ጊዜ ያገለገለውን የክፍለ ሀገራዊ አስተዳደር፤ ለመሬት ነጠቃ እንዲያመቻቸው ሲሉ፤ በማንአለብኝነት በማፈራረስ ሀገሪቱ አሁን ላለችበት የማያቋርጥ የእርስ በርስ ትርምስና ፍጅት ዳርገዋታል።

ጠቅላይ ምኒስትሩ ፍቅርን መምከራቸው መልካም ነው። ነገር ግን፤ የፍቅር ምክር ብቻውን ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ ሊሆን አይችልም። መፍትሔው፤ የታጠፈውን የክፍለ ሀገራዊ አስተዳደር መልሶ መዘርጋትና እያንዳንዱ ክፍለሀገር ፌደራላዊ ራስገዝ አስተዳደር እንዲሆን ማድረግ ነው።

ጠቅላይ ምኒስትሩ፤ ይህን ሀሳብ በሥራ ላይ ለማዋል በዙሪያቸው ካሉት ብሔርተኞች የፖለቲካ ድጋፍ ላያገኙ ይችሉ ይሆናል። ምክንያቱም፤ ሀሳቡ የእነዚህን ቡድኖች የግል ጥቅም መንካቱ አይቀርም። ለምሳሌ፤ የትግሬ ብሔርተኞች ያለአግባብ ከወሎና ከጎንደር የነጠቁትን መሬት መመለስ ሲገባቸው፤ የወታደር ኃይላቸውን መከታና ማስፈራሪያ በማድረግ፤ ይኸው እስከዛሬ መሬቱን ይዘው ተቀምጠዋል።

ጠቅላይ ምኒስትሩም ይሁኑ በዙሪያቸው ያሉት ብሔርተኞች፤ በፈቃዳቸው ኢትዮጵያን ወደ ታሪካዊው ክፍለሀገራዊ አስተዳደር ይመልሳሉ ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው። ሀገሪቱ ወደ ክፍለሀገራዊ አስተዳደርና ኢትዮጵያዊ አንድነት ልትመለስ የምትችለው ብሔርተኞችን ለመቋቋም የሚችል የኢትይጵያዊነት ኃይል ሲኖር ብቻ ነው።

ላለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት፤ ገዢው መንግሥት፤ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ከሀገሪቱ ውስጥ ጨርሶ እንዲጠፋ ማድረጉ ይታወቃል። ለምሳሌ፤ በብሔር እንጂ በኢትዮጵያዊነት መታወቅ ተከልክሏል። የኢትዮጵያን ስም የያዙ የፓለቲካ ፓርቲዎች ህጋዊ እውቅና አይሰጣቸውም። መሪዎቻቸው ታስረዋል፤ በግፍ ተገድለዋልም። አንዳንዶቹም፤ ሳይወዱ በግድ፤ ብሔርተኛ የሆነውን ህገመንግሥት እንዲቀበሉና በዘር ፓርቲነት እንዲመዘገቡ ተደርገዋል።

ይህ ሁሉ በደል ቢፈጸምም፤ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ጨርሶ ሊጠፋ አልቻለም። ምክንያቱም፤ ኢትዮጵያዊነት በተለያዩ ብሔሮች ውስጥ ከብዙ ጊዚ ጀምሮ ተሰርጾ የቆየ ስሜት በመሆኑ ነው። በአሁኑ ሰዓትም፤ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እየተጠናከረ በመሄድ ላይ ይገኛል። በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር፤ የነባሩ አረንጓዴ-ብጫ-ቀይ ሰንደቅ ዓላማ በይፋ መውለብለብ ለዚህ አንዱ ምስክር ነው።

የኢትዮጵያዊነት ኃይል መጠናከር ለሀገሪቱ ጠቃሚነት አለው። ምክንያቱም፤ የአንድ ወገን ብቻ ማየል ህብረተሰቡን ይጎዳል። ለምሳሌ፤ ዛሬ የኢትዩጵያን ደህንነትና ቀጣይነት አደጋ ላይ የጣለው፤ የብሔርተኞች ኃይል በብቸኝነት ማየል ነው።

ስሊዚህ፤ ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት ብሔርተኝነት ወደዲሞክራሲያዊ አንድነት በማሸጋገር ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማምጣት የሚቻለው፤ ሁለቱም ኃይሎች ተመጣጣኝ ሲሆኑና፤ የዛሬውንም ሆነ የወደፊት ችግሮቻቸውን በእኩልነትና በመደራደር ለመፍታት የሚያስችል ሚዛናዊ አወቃቀር ሲፈጠር ብቻ ነው።