የኢትዮጵያዊያን በግፍ መገደልና መፍትሄው

ዶ/ር ዳንኤል ተፈራ

የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር፤ ኤመረተስ

የጊዜውን ፖለቲካ በመከተል፤ “አማራ ተገደለ” ወይም “ክርስቲያን ተገደለ” ከማለት ይልቅ በግፍ የተገደሉት ኢትዮጵያዊያን ናቸው ማለት ትክክል ይሆናል። ላለፉት ሃያዘጠኝ ዓመታት በተለይ በኦሮሞና በሲዳማ ክፍለሀገራት ውስጥ በግል ሥራ ተሰማርተው በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ ከፍ ያለ በደል ተደጋግሞ ተፈጽሟል። ከሀገሬው አልተወለዳችሁም በመባል፤ አርሰው እንዳይበሉ መሬት ተነፍገዋል፤ ጽፈው ወይም ውትድርና ተቀጥረው እንዳይኖሩ ከቢሮክራሲው ታግደዋል።

እነዚህ በገዛ ሀገራቸው ባይተዋር የተደረጉ ኢትዮጵያዊያን ያላቸው ምርጫ በንግድና በሌላ ጥቃቅን ሞያዎች መተዳደር ብቻ ነው። ይህን የምናገረው በርቀት አሜሪካን ተቀምጬ ሳይሆን፤ በተደጋጋሚ ከስፍራው በመሄድ ከሰበሰብኩት እውቀት በመነሳት ነው። ከዚያም በላይ፤ የዛሬ ሰባአራት ዓመት እትብቴ የተቀበረው በይርጋ ዓለም ከተማ፤ በሲዳማ አውራጃ ስለሆነ፤ የደቡቡን ክፍል ጠንቅቄ አውቀዋለሁ።

ሰሞኑን በአዳሚቱሉ፤ በዝዋይና በሻሸመኔ በኢትዮጵያዊያን ላይ አሰቃቂ ግድያዎች ተፈጽመዋል። በሶሻል ሚድያ እንደተሰራጨው ሁሉ፤ ለምሳሌ በአዳሚቱሉ፤ ከአንድ ቤተሰብ፤ አምስት ሰዎች በገዛ ቤታቸው ውስጥ፤ ለአንድ ሰዓት ያህል በዱላ ተደብድበው፤ በገጀራ ተጨፍጭፈው ሲገደሉ፤ መንግሥትም ይሁን ሌላ አካል አልደረሰላቸውም። በሠለጠነው ሀገር፤ መንግሥት ህዝብን ነቅቶ ይጠብቃል። ህዝቡም በቤቱ ውስጥ እራሱን ከወንጀለኞች እንዲከላከል በህግ የተደነገገ መሣሪያ የመያዝ መብት አለው።

ብሄርተኞች በጦር ኃይል ሥልጣን ከጨበጡበት ጊዜ አንስቶ፤ ኢትዮጵያዊያን፤ በተለይ በገጠር የሚኖሩ፤ በእኩልነት የመኖር ዋስትና  አላቸው ለማለት አያስደፍርም። በህወሀትም ጊዜ ይሁን በአሁኑ ሰዓት፤ ሀገሪቱን የሚገዛው ያው የብሄርተኞች መንግሥት ነው። ህገመንግሥቱም የብሄርተኞች ህገመንግሥት ነው። ኢትዮጵያዊያንን አያቅፍም።

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለወጠው የፖለቲካው ዘዴ እንጂ፤ የብሄር በላይነት አይደለም። ለምሳሌ፤ ከዚህ በፊት የወያኔ ብሄርተኞች ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ሲያጥላሉ፤ የዛሬዎቹ የኦህዴድ ብሄርተኞች ደግሞ ስሙን እየደጋገሙ ያነሱታል። ስለዚህ፤ ባለማወቅም ይሁን ለግል ጥቅም በመሸነፍ፤ ጥቂት የማይባሉ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን ብሄርተኛ መንግሥት ይደግፋሉ። ገዢው መንግሥትም ይህን ከለላ በማድረግ ”ነፃነት ደህና ሰንብች“ ብሎ የፖለቲካ ተቃዋሚዎቹን ሰብስቦ አስሯል።

በተለይ የአቶ እስከንድር ነጋን መታሰር ለማመን ያዳግታል። ለምሳሌ አቶ እስክንድር ነጋ፤ ባለፈው ዓመት በሰሜን አሜሪካና አውሮፓ በመዘዋወር “ከቀበሮ ጉድጓድ ነው የመጣሁት። የዘር ማጥፋት አደጋ በሀገሪቱ ላይ እያንጃበበ ነው” በማለት ኢትዮጵያዊያንን እንዲሁም ዓለምአቀፍ ድርጅቶችን ማስጠንቀቃቸው ሲታወቀ፤ መንግሥት ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረጉ አማጺ ብሄርተኞች በህይወትና በንብረት ላይ ከፍ ያለ ጥፋት ሊየደርሱ ችለዋል። እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ፤ አቶ እስክንድርን  በዘር ጥላቻ መወንጀልና ማሰር፤ በግፍ ለተገደሉት ኢትዮጵያዊያን መንግሥትን ከተጠያቂነት ነፃ አያደርገውም።

ገዢው መንግሥት ባልደራስን አጥብቆ ይጠላዋል። ለምን? ድምፁን ለተነፈገው የአዲስ አበባ ህዝብ በሰላማዊ መንገድ የሚሟገት ድርጅት ነው፤ ባልደራስ። ለሰው ልጆች የተፈጥሮ መብት በሰላሚዊ መንገድ መታገል በዓለም ድርጅቶች ዘንድ የተደነገገ ነው። ነገር ግን፤ እኔን ካልደገፋችሁ በማለት፤ ገዢው መንግሥት “ጦርነት እንገጥመዋለን” ብሎ ባልደራስን ማስፈራራቱን  እናስታውሳለን። ይሁንና፤ ከመንግስት እንዲሁም ከደጋፊዎቹ ተጽእኖና ማስፈራሪያ  ቢገጥመውም፤ ባልደራስ ዓላማውን አልቀየረም፤ እራሱን ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት ከመለወጡ በስተቀር። ባልደራስ ከሌሎች ሲነጻጸር የህዝብ ድጋፍ አለው ለማለት ይቻላል። ለምሳሌ፤ የተቀሩት ፖለቲከኞች በመትረየስ ታጅበው ሲሄዱ፤ የባልደራስ መሪዎች በህዝብ መሀል ያለፍርሀት ይዘዋወራሉ።

አቶ እስክንድር ነጋ በኢትየጵያዊያን ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ አስቀድመው ማሳሰባቸው ያስመሰግናቸዋል እንጂ አያሳስራቸውም። በቅርቡ በተደረጉት ሰላሚ ሰልፎች ላይ “የእስክንድርን ስም አታንሱ” ሲሉ መሪዎች ተደምጠዋል። በውጪ ሀገር የሚኖሩ ታዋቂ ሰዎችም “ከኢትዮጵያ ማንም አይበልጥም” ኢትዮጵያን ማዳን ይቀድማል እያሉ ተሟግተዋል። በሀገር ቤት ውስጥ ያሉ አንዳንድ ምሁራን፤ “ከእንግዲህ በኋላ መንግሥት ክንዱን ማጠንከር ብቻ ነው ያለበት” እያሉ አሳስበዋል። እነዚህ ሁሉ የገዢው መንግሥት ደጋፊዎች ናቸው። ይህን ማድረግም መብታቸው ነው። ነገር ግን፤ እራሳቸውን ለመጥቀም ሲሉ፤ በሚናገሩትም ሆነ በሚሠሩት ሌላውን መጉዳት የለባቸውም።

ገዢው መንግሥት ከፍተኛ ኃይል በእጁ የያዘ ነው። ይሁንና፤ ኃይል ያለው፤ ኃይል የሌለውን አስሮ ለፍርድ ማቅረብ፤ ቂምበቀል እንጂ ፍትህ አይደለም። ከዚህ ሁሉ ይልቅ ወደመሠረታዊው ችግር ማተኮር ይበጃል። ኢትዮጵያዊያንን በየጊዜው በግፍ የሚያስገድለው፤ ለብሄርተኞች ጥቅም ብቻ ታቅዶ የተቀረፀው እራሱ ህገመንግሥቱ ነው። ብሄርተኞችንና ኢትዮጵያዊያንን እኩል የሚያቅፍ ዲሞክራሲያዊ ህገመንግሥት ያስፈልጋል። ይህ ሊሆን የሚችለው ግን በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በገዢው መንግሥት ላይ ጠንካራ ግፊት ሲያደርጉ እንጂ፤ ስረመሠረቱ ብሄርተኛ ለሆነ መንግሥት፤ ወያኔም ይምራው ኦህዴድ፤ ድጋፍ በመስጠትና አምባገነንትን በማዳበር አይደለም። ያለበለዚያ በየጊዜው በግፍ ለሚጊደሉት ኢትዮጵያዊያን፤ ተጠያቂው ገዢው መንግሥት ብቻ ሳይሆን ደጋፊዎቹም ናቸው።